የህገ- መንግስት አጣሪ ጉባኤ እጩ አባላት እንዲሾሙ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ጸደቀ

66

ታህሳስ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የህገ- መንግስት አጣሪ ጉባኤ እጩ አባላት እንዲሾሙ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ጸደቀ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው እለት ሶስተኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል።

በህገ መንግስቱ አንቀጽ 82 ንዑስ አንቀጽ 2 ፊደል ተራ ቁጥር "ሐ" መሰረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት በሪፐብሊኩ ኘሬዚዳንት የሚሾሙ በሙያ ብቃታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው ስድስት የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሾሙ ይታወቃል።

በህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ቀደም ሲል የተመረጡት አባላት የአገልግሎት ጊዜያቸው በሐምሌ 20 ቀን 2013 ዓ.ም ተጠናቋል።በመሆኑም በምክር ቤቱ በሙያ ብቃታቸው እና በስራ ልምዳቸው የቀረቡት እጩዎች በሪፐብሊኩ ኘሬዚዳንት የሚሾሙ በመሆኑ በዛሬው እለት በ4 ተቃውሞ በ12 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ 11 አባላት ሲሆኑ 6ቱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርቡ ናቸው።

በህገ - መንግስቱ አንቀጽ 82 እንደተቀመጠው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አሥራ አንድ አባላት ይኖሩታል፡፡ጉባኤውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንት በሰብሳቢነት እንዲሁም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ኘሬዚዳንት በምክትል ሰብሳቢነት ይመሩታል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት በሪፐብሊኩ ኘሬዚዳንት የሚሾሙ በሙያ ብቃታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው ስድስት የሕግ ባለሙያዎችም ይኖሩታል።

ምክር ቤቱ እያካሄደ በሚገኘው መደበኛ ስብሰባ ለፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባልነት የቀረቡለትን ዕጩ የጉባኤ አባላት በ13 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እንደሚመራ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም