በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች ማቋቋም ቀዳሚ ተግባራችን ነው

256

ዲላ፤ ታህሳስ 6/2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች ማቋቋም ቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑን የጌዴኦ ዞን ሴቶች ገለጹ።

አሸባሪውን ህወሓት የፈጸመውን ግፍ የሚያወግዝና የበቃ /No More/  ዘመቻ አካል የሆነ የተቋውሞ ሰልፍ ዛሬ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።

ከሰልፈኞቹ መካከል ወይዘሮ ወገኔ ገመዳ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት  በሴቶችና ህጻናት ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ፈጽሟል።

የአሸባሪው የግፍ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን ለማቋቋም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ወይዘሮ ዘመናይ ህርባዬ በበኩላቸው አሸባሪው በከፈተው ጦርነት በአማራና በአፋር ክልሎች ህጻናትና አረጋዊያን የመደፈርና ሌሎች ጥቃቶች ሰለባ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሰሩ አለም አቀፍ ተቋማት የአሸባሪውን ህወሓት አጸያፊ ተግባር ሊያወግዙ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዘግናኝ ድርጊቱን ከማውገዝ ባለፈ የተሻለች ሀገር በመገንባት የኢትዮጵያን ጠላቶች ማሳፈር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ”በአሸባሪው ህወሓት ለጉዳት የተዳረጉ ሴቶችን ማቋቋም ተቀዳሚ ተግባራችን ነው” ብለዋል።

“አሸባሪው ህወሓት በንጹሃን ወገኖች ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋ ተስፋ መቁረጡንና ለመጥፋት መቃረቡን የሚያሳይ ነው” ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ እቴነሽ በየነ ናቸው።

አሸባሪው ህወሓት ዳግም የሀገርም ሆነ የሴቶችና ህጻናት ስጋት እንዳይሆን ለተጀመረው ሀገር የማዳን ተግባር ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የዞኑ ሴቶች ለሰራዊቱ ደጀን ከመሆንና አካባቢያቸውን በንቃት ከመጠበቅ ባለፈ አንድ እቃ ለአንድ ቤተሰብ በሚል የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ የተጀመረውን  ዘመቻ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በአሸባሪው ህወሓት የሚፈጸም ግፍና በደልን በዝምታ ማለፍ ተገቢ አለመሆኑን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ክልል የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ የምስራች ገመዳ ናቸው።

“የህልውና ዘመቻውን ከመደገፍና አሸባሪውን ህወሓት ከማውገዝ ባለፈ የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት በቃ ማለታችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን” ብለዋል።