በህገወጥ መንገድ የተከማቸና ሲጓጓዝ የነበረ ቡናና ልባሽ ጨርቅ ተያዘ

168

ጎባ ታህሳስ 6/2014 (ኢዜአ) ግምቱ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ቡናን ጨምሮ 130 ቦንዳ የኮንትሮባንድ ልባሽ ጨርቅ መያዙን የሮቤ ከተማ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ እዝ አስታወቀ።

የእዙ አባል የሆኑት የሮቤ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ዳይሬክተር ኮማንደር መርጋ ገርቢ ለኢዜአ እንደገለጹት ቡናውና ልባሽ ጨርቁ የተያዘው ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተካሄደ ፍተሻና ቁጥጥር ነው።

ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በግለሰቦች ቤት በተካሄደ ድንገተኛ ፍተሻ በህገወጥ መንገድ የተከማቸ 200 ኩንታል ቡና መገኘቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም  5 ሺህ ቋሚ የጽድ እንጨትና ሌሎች የደን ውጤቶች ተከማችተው መገኘታቸውን አመልክተዋል።

ቡናና የደን ውጤቶችን ደብቀው የተገኙ ግለሰቦች ጉዳይ በህግ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኮማንደር መርጋ ገለጻ የተያዘው ቡና ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ነው።

በተመሳሳይ  የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 -18622 አ.አ በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሸከርካሪ  ተጭኖ ወደ መሀል ሀገር ሲጓጓዝ የነበረ 130 ቦንዳ ኮንትሮባንድ ልባሽ ጨርቅ መያዙን ተናግረዋል።

አሽከርካሪው ለጊዜው በመሰወሩ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል እያሳየ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጠል ኮማንደር መርጋ ጠይቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም