ኀብረተሰቡ በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ

57

ታህሳስ 6/2014/ኢዜአ/ ኀብረተሰቡ በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ፡፡

ይህንን ወቅት በመተባበር እና በመደጋገፍ ማለፍ እንደሚገባም ነው የሃይማኖት አባቶቹ የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አባል ሀጅ ሙሀመድ መሀመድ ካለንበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋሙ ስራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን የፈረሱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ትብብር ማድረግ እንዳለባቸውም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

የአማራ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪ አቶ ፋሲል ታዬ በበኩላቸው አሸባሪው የህወሃት ቡድን በርካታ መሰረተ ልማቶችን ማውደሙን አንስተዋል።

ህብረተሰቡን ወደ መደበኛው ኑሮው ለመመለስ ከመንግስት በተጨማሪ የኃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ዋና ጽህፈት ቤት ተወካይ ዶክተር ታረቀኝ ያቆብ በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን መልሶ የማቋቋሙ ስራ በቤተክርስቲያኗ እንደ አገልግሎት የተያዘ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

ምእምኑ በመልሶ ማቋቋም ስራ እንዲሳተፍ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሀሉም ዜጋ በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖቹን የመርዳት ኃላፊነት እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የባህርዳርና ደሴ አቃቤ መንበርና የሰበካ ጉባኤ ማህበራዊ ልማት ኃላፊ አባ ስንታየሁ ገላው ናቸው።

የሃይማኖት አባቶች በዜጎች ዘንድ የእርስ በርስ መረዳዳት ባህል እንዲጎለብት ማስተማር እንዳለባቸውም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም