የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሴቶች ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ አደረጉ

58

ጎንደር ፤ ታህሳስ 6/2014(ኢዜአ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሴቶች ''ሴቶች ከደጀን እስከ ግንባር'' በሚል ለህልውና ዘመቻው ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ አዘጋጅተው ወደ ግንባር መላካቸውን የዞኑ የማህበረሰብ ስንቅ ዝግጅት አስተባባሪ አስታወቀ፡፡

የሽብር ቡድኑ ግብዓተ መሬት እስኪፈጸም ድረስ በስንቅ ዝግጅትም ሆነ በገንዘብ መዋጮ ለሰራዊቱ እያደረጉት ያለው  ድጋፍ  እንደማያቋርጡም የዝግጅቱ ተሳታፊ ሴቶች ተናግረዋል፡፡

የዝግጅቱ አስተባባሪ የሆኑት የዞኑ ሴቶችና ህጻናት መምሪያ  ኃላፊ ወይዘሮ ቀኑ ቢያድግልኝ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የህልውና ዘመቻውን በድል ለማጠናቀቅ ሴቶች በሁሉም ግንባር እየተሳተፉ ይገኛል።

በስንቅ ዝግጅትም በዞኑ 15 ወረዳዎች አደረጃጀት የታቀፉ ከ60 ሺህ በላይ ሴቶች እየተሳተፉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ሴቶች ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን በማስተባበር ባደረጉት ርብርብ ደረቅ ስንቅና ሌሎች የአይነት ድጋፎች በማዘጋጀት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ወደ ግንባር ልከዋል ነው ያሉት።

በሽብር ቡድኑ ወረራ ሳቢያ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል 300 ኩንታል አልባሳትና 426 ጥንድ ጫማዎችንም በማሰባሰብ በደባርቅ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ ማድረጋቸውን ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ተሰባስቦ የተላከው ደረቅ ስንቅና ሌሎች ምግብ ነክና አልባሳት ድጋፍ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

ለተፈናቃይ ወገኖች ወርሃዊ ቀለብ የሚውል 34 ሺህ 426 ኩንታል እህል በማሰባሰብ በአሁኑ ወቅት ወዳሉበት መጠለያ ለመላክ ዝግጅት በመደረግ ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

''ወራሪው የሕወሃት የሽብር ቡድን በሴቶችና ህጻናት ላይ የፈጸመው ግፍና በደል ከምንም በላይ ያንገበግበኛል'' ያሉት ደግሞ በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ የጯሂት ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አዛለች መኮንን ናቸው፡፡

የሽብር ቡድኑን ለሚፋለመው ሰራዊት አይደለም በግንባር በመዝመት የንጹሃንን ሰቆቃና እንግልት እንዲያቆም በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን ለመወጣት  ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

በዚህ  ከተማ የመንግሰት ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ አባይነሽ ደጉ፤ ሀገርን ለማፍረስ የተነሳውን ወራሪ ጠላት የጥፋት ተግባር ለመቀልበስ በግንባር ለዘመቱ የጸጥታ ሃይሎች የሚውል ስንቅ በማዘጋጀት ድጋፋቸውን እንዳላቋረጡ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በፊት የወር ደመወዜን ለግሻለሁ፤ ዛሬ ደግሞ በሴቶች አደረጃጀት በነፍስ ወከፍ እስከ 500 ብር ለግሼ ዳቦ ቆሎና በሶ ለማዘጋጀት በጉልበቴ ጭምር እየተሳተፍኩ እገኛለሁ ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ግብዓተ መሬት እስኪፈጸም ድረስ በስንቅ ዝግጅትም ሆነ በገንዘብ መዋጮ ለሰራዊቱ እያደረጉት ያለው ህዝባዊ  ድጋፍ  አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የዝግጅቱ ተሳታፊ ሴቶች የተናገሩት፡፡

የውጭና የውስጥ ጠላቶች በሀገራችን ላይ የደቀኑትን አደጋ ለመቀልበስ ሀብት በማሰባሰብ ፣ ሰራዊቱንና ተፈናቃይ ወገኖችን በመደገፍ፣ ፣ የዘማች  ቤተሰብ በመንከባከብ፣ በስንቅ ዝግጅትና አቅርቦት እንዲሁም የአካባቢ ሰላም በመጠበቅና በሌሎች ግንባሮች ኢትዮጵያዊያን ተሳትፏችንን አጠናክረን ማስቀጠል  ይጠበቅብናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም