የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ስብሰባ መጥራቱ የተቋሙን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው

83

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 06/2014(ኢዜአ)  የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያደርገው ስብሰባ የተቋሙን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ፤ በሰጡት መግለጫ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምከር የጠራውን ልዩ ስብሰባ የአፍሪካ አገራት ስብሰባውን አለመደገፋቸውን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ እውነትን የካደ ጫና ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው ሰሞኑንም በኢትዮጵያ ጉዳይ ስብሰባ መጥራቱ የተቋሙን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ አስገብቷል ብለዋል።

የምክር ቤቱ ስብሰባ የተወሰኑ መንግስታትን ፍላጎት ለማስፈፀም የሚካሄድ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው ተቋሙም በእነዚህ መንግስታት ተፅዕኖ ስር ወድቋል ነው ያሉት፡፡

የምክር ቤቱ ዓላማ የአፍሪካዊያን ችግር በአፍሪካዊያን እንዳይፈታ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በርካታ የአፍሪካ አገራት በአባልነት በሚያገኙበት ምክር ቤት ቢሆንም በተጠራው ልዩ ስብሳባ ላይ አንድም የአፍሪካ አገር ያልደገፈው መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋር እና በአማራ ክልሎች በርካታ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲፈጽም ምክር ቤቱ ዝምታን መምረጡም የተቋሙን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል።

አሸባሪው ሕወሓት የፈጸማቸውን የጅምላ ግድያና ሌሎች አሰቃቂ ወንጀሎች የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብኣዊ መብት ምክር ቤት በዝምታ ማለፉ ትዝብት ላይ ጥሎታልም ነው ያሉት።

በአዲስ አበባ ተቀማጭነታቸውን ያደረጉ አንዳንድ ኤምባሲዎች ማስፈራረያ የሚመስሉ ማስጠንቀቂያ ሲያወጡ እንደነበር ጠቅሰው አሁን ላይ ግን እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል።

የ"በቃ (#NoMore)" ዘመቻ በዓለም ዙሪያ በተለይም በጃማይካ፣ በአውስትራሊያ፣ በአሜሪካ፣ በዴንማርክ፣ በኖርዌይና ሌሎችም አገራት ትላልቅ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች መካሄዳቸውን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ጦርነት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ወይም በጥቁር ህዝቦች ላይ የሚደረግ ጦርነት መሆኑ የተንፀባረቀበት ዘመቻ እንደነበርም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም