አፍሪካ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ የተጀመረው እንቅስቃሴ ፍትሐዊ ዓለም የመፍጠር ትግል ነው

124

ታህሳስ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ የተጀመረው እንቅስቃሴ አዲስና ፍትሐዊ ዓለም የመፍጠር ትግል አካል እንደሆነ በአሜሪካ ስቶኒብሩክ በሚገኘው የኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ፖለቲካና ታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ሽመልስ ቦንሳ ገለጹ።

ኢትዮጵያ አፍሪካውያንን ከሁለንተናዊ ጫና ነጻ የማውጣት ትግሉን በተጠናከረ መልኩ በማካሄድ በአፍሪካ ያላትን ታሪካዊ ስፍራ ይዛ መቀጠል እንዳለባትም አስገንዝበዋል።

አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ማግኘት አለባት የሚለው ጥያቄ የረጅም ጊዜ ታሪክ መሰረት ያለው መሆኑን ያስታወሱት ዶክተር ሽመልስ፤ የአፍሪካ የነጻነት አባቶች አህጉሩ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ ማግኘቱ የፍትሐዊነትና እኩልነት ጥያቄ መሆኑን በማስታወቅ ትግል ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

አሁንም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድና ሌሎች የአህጉሩ መሪዎች ጥያቄውን ማንሳታቸው ከፍትሃዊነትና ከእኩልነት የመነጨ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የጸጥታው ምክር ቤት ሲቋቋም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊዎችን ፍላጎት የማስጠበቅ አላማ የነበረውና የተቀረውን ዓለም የማይወክል እንደሆነ ገልጸዋል።

በአፍሪካ የነጻነት አባቶች የተጀመረው ትግል አሁን እንደ አዲስ መቀስቀሱ ትግሉን በዓለም ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ውጤታማ ሊያደርጉት የሚችሉ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ሰአት የዓለም የፖለቲካ አሰላለፍ በመቀየሩ ምክንያት ብዙ የሃይል ስብስቦች በመፈጠራቸው ጥያቄው ተቀባይነት የማግኘት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

አፍሪካውያን በአሁኑ ሰአት የራሳችንን እጣ ፈንታ በራሳቸውን መወሰን አለብን በሚል ለፍትሐዊነትና ለእኩልነት እያደረጉት ያለው አዲስ ትግል የምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንቅስቃሴውን እንዲቀጣጠል የሚያደርግ መሆኑንም አመልክተዋል።

“የተጀመረው እንቅስቃሴ በምዕራባውያን ፍልስፍና የተቃኘውን የዓለም አካሄድ በመቀየር አዲስና ፍትሐዊ ዓለም የመፍጠር ትግል አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል” ብለዋል።

“ኢትዮጵያ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ ማግኘት አለባት የሚለውን እንቅስቃሴ መቀላቀሏ በታሪክ በአፍሪካውያንና በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ካላት ተቀባይነት አንጻር ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው” ብለዋል ዶክተር ሽመልስ።

ኢትዮጵያ አፍሪካን ነጻ ለማውጣት የጀመረችው ትግልም ለአፍሪካውያንና ለሌሎች የተጨቆኑ ሕዝቦች መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ትግሉን በተጠናከረ መልኩ በማካሄድ በአፍሪካ ያላትን ታሪካዊ ስፍራ ይዛ መቀጠል እንዳለባትና ይሄን ካደረገች አፍሪካውያንን አንድ የማድረግ አቅም እንደሚፈጠር ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አፍሪካ የሚገጥሟትን ፈተናዎችን መቋቋምና መሻገር የምትችልባቸውን አማራጮች የቃኘ አፍሪካ ተኮር የሆነ የውጭ ፖሊሲ ልትቀርጽ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አፍሪካውያን በነጻ የንግድ ቀጠና ጨምሮ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ለመዋሃድ የጀመሩት እንቅስቃሴ የጋራ ራዕይ እንዲፈጠር የማድረግ ጥቅም ስላለው በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

አህጉሩ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖረው የተጀመረው እንቅስቃሴ የነጻነት፣ የእኩልነትና የፍትሐዊነት ትግል በመሆኑ አፍሪካውያን መቀላቀል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የሚደረገው ትግል ዘርፈ ብዙና ረጅም ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም አፍሪካውያን አንድ ከሆኑ በአሸናፊነት እንደሚወጡት ዶክተር ሽመልስ አክለዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም