ሀገርአቀፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሌሎችን ባህልና ማንነት በማወቅ ሀገራዊ መግባትን ይፈጥራል፤-በጎፈቃደኞች

63
ሃዋሳ ነሀሴ 18/2010 አገር አቀፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሌሎችን ባህል በማወቅ ሀገራዊ አንድነትና መግባባትን ለማምጣት እንደሚያስችል  የበጎ ፈቃድን በደቡብ ክልል  ያከናወኑ ወጣቶች ገለጹ፡፡ በደቡብ ክልል በተያዘው የክረምት ወቅት ከ1 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰማራታቸውን  የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡ በደቡብ ክልል በአገር አቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ለኢዜአ እንደገለጹት ቀደም ሲል አገልግሎቱን በትውልድ አካባቢያቸው የሚያከናወኑ በመሆኑ ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር የመገናኘትና ባህል የመለዋወጥ አጋጣሚ አልነበራቸውም፡፡ ከአርባምንጭ እንደመጣ የሚናገረው ወጣት ታምራት አብርሀም እንዳለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከአካባቢው ውጭ የማከናወን እድል አጋጥሞት አያውቅም፡፡ እዚህ የተሰባሰብን ከተለያየ ክልል የመጣን በመሆኑ ደቡብ ማነው የሚለውን በሚገባ ከማወቅ በላይ እርስ በእርስ ያለንን አንድነትና ትስስር ያጠናክራል ብሏል፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከክረምት በተጨማሪ በበጋም ጭምር ሊለመድ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን እንደመጣች የተናገረችው ወጣት ደበቁ ቶላ እንዳለችው ለበጎፈቃድ ስራ መሰማራታቸው ለህብረተሰቡ ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በተጨማሪ የእርስ በእርስ ትውውቁን በማጎልበት ኢትዮጵያዊ አንድነትን ያጠናክራል፡፡ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ያለው የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ በመሆኑ  የህብረተሰቡ ግንዛቤ በማሳደግ ችግሩን መቅረፍ ይገባል ብላለች፡፡ በአገር አቀፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የራሷን ድጋፍ ለማድረግ ወደ ክልሉ መምጣቷ በሀዋሳ ከሚኖሩ ህዝቦች ብዙ ቁም ነገር መቅሰሟን ገልፃለች፡፡ ከአማራ ክልል ጎንደር ከተማ እንደመጣ የገለጸው ወጣት ይንገስ ጸጋዬ በበኩሉ ወጣቱ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሲገባ ወይም በስራ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ከአካባቢው የሚወጣበት አጋጣሚ ባለመኖሩ ከተለያየ ማህበረሰብ ጋር የመተዋወቅ፣ የልምድና የባህል ልውውጥ ማደረግ ሳይችል እንደቆየ ገልጿል፡፡ በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ እህመድ የመደመር መርህ መሰረት አገር አቀፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መኖሩ እርስ በእርስ በመተዋወቅ ትስስርና አንድነትን ለማጠንከር የሚያስችል እድል መፈጠሩን ተናግሯል፡፡ የደቡብ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ እንደገለጹት ከክልሉ ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተመለመሉ 150 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በአገር አቀፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉ መላካቸውን ገልፀዋል፡፡ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ 207 ወጣቶች ደግሞ በሀዋሳና በሶዶ ተመድበው አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ወጣቶቹ ከሀዋሳና ከወላይታ ሶዶ ባለፈ በሀድያ፣ ከንባታና ጠንባሮ ስልጤና በጉራጌ ዞን በመገኘት የደም ልገሳ፣ የአካባቢ ጽዳት፣ የችግኝ ተከላ የማጠናከሪያ ትምህርትና ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ ወጣቶቹ በክልሉ ውስጥ የተለያዩ ስራዎችን መስራታቸው መቀራረብና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከሩን ጠቁመዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም