የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሠብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

155

ታህሳስ 6/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአሸባሪው የህወሓት ወራሪ ለተፈናቀሉ የአፋር ክልል ወገኖች የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሺፈራው ተሊላ፤ በአፋርና በአማራ ክልሎች በሽብርተኛው ህወሓት ወራሪ ውድመት የደረሰባቸውን የኤሌክትሪክ መስመሮች ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በቅርብ ቀናትም ከኮምቦልቻ ሰመራ ያለው የኤሌክትሪክ መስመር ጥገና ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የክልሉን ሁለንተናዊ ልማት ለማሳለጥ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግንባታውን እያሰፋ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ተቋሙ ሽብርተኛውን የህወሓት ወራሪ እየተፋለመ ለሚገኘው ጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት 61 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማድረግ ደጀንነቱን ማሳየቱን አቶ ሺፈራው ገልጸዋል።

የአፋር ክልል ፕሬዚደንት አወል አርባ፤ የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ካለው ከንቱ ቅዠት የተነሳ በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም በርካታ ዜጎችን ማጎሳቆሉን አንስተዋል።

የሽብር ቡድኑን ወራሪ ከአፋር እንዳይወጣ ለማድረግ ልዩ ኃይሉና ሚኒሻ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጋር ተቀናጅተው አንጸባራቂ ድል ማስመዝገባቸውንም አስታውሰዋል።

አቶ አወል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአሸባሪው ወራሪ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ላበረከተው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።