ጅማ ዩኒቨርሲቲ የዓይን ሞራ ቀዶ ህክምና በነፃ እየሰጠ ነው

201

ጅማ ፤ታህሳስ 5/2014 (ኢዜአ) ጅማ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የዓይን ሞራ ቀዶ ህክምና በነፃ እየሰጠ ነው፡፡

የነፃ ህክምናው በዩኒቨርሲቲው የዓይን ህክምና ትምህርት ክፍል አስተባባሪነት እና በ“ላይት ፎር ዘ ዎርልድ፣ ሂማልያን ካታራክት እና ፍሬድ ሆሎውስ ፋውንዴሽን” ድጋፍ የሚሰጥ ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲው  የዓይን ህክምና ትምህርት ክፍል ሃላፊ ዶክተር  ጃፋር ከድር እንደገለጹት፤ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ችግር በጅማ ዞንም ሆነ በሌላው የሀገሪቱ አካባቢዎች በስፋት ይገኛል።

ይኸም በአብዛኛው ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሆኖ ለእይታ መቀነስና ለዐይነ ስውርነት የሚዳርግ በሽታ መሆኑን ገልጸው፤ ህክምናውም ለአንድ ሰው  ከአራት ሺህ ብር በላይ ወጪ  የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ለአስር ቀናት በሚቆየው የነፃ ህክምናው በጅማ ከተማና በዞኑ ባሉ ወረዳዎች ለሚገኙ 1 ሺህ ታካሚዎች ተደራሽ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም   እስከ አራት ሺህ ለሚደርሱ ሰዎች የምርመራ፣ መለስተኛ ህክምናና ሌሎች አገልግሎቶች እንደሚሰጥም ተመልክቷል፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር  ጀማል አባፊጣ  በበኩላቸው፤ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ  የማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ካሉበት ወረዳ ትራንስፖርት አመቻችቶ በማምጣት እንዲታከሙ እያደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም የምግብና መኝታ አገልግሎቶችን በማዘጋጀት እንዲሁም ከህክምና በኋላ ወደ መጡበት ስፍራ ለመመለስ ተቋሙ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ከታካሚዎች መካከል  አባመጫ አባገሮ በሰጡት አስተያየት፤ ባገኙት ነፃ የህክምና አገልግሎት ከወጪና ከእንግልት ተላቀው ብርሃናቸው በመመለሱ መደሰታቸው በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል።

ወይዘሮ አበራሽ ማሞ በበኩላቸው፤  ከጊዜ በኋላ ማየት እየቸገራቸው መቆየቱንና በነፃ ለመታከም እድሉን በማግኘታቸው እንደተደሰቱ ነው የገለጹት።

የዓይን ህክምና ትምህርት ክፍሉ ከዚህ በፊትም መሰል አገልግሎቶችን በነፃ በመስጠት በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን  ተጠቃሚ ማድረጉም ተመልክቷል።