የጥበብ ሰዎች በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ የመገንባት ማህበራዊ ኃላፊነት አለባቸው

137
አዲስ አበባ ነሀሴ 18/2010 የጥበብ ሰዎች በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ የመገንባት ማህበራዊ ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ የዘርፉ አንጋፋ ባለሙያዎች ገለፁ። የጥበብ ባለሙያዎች ሥራ በግለሰቦች ህይወት እየሰረጸ የትውልድን አስተሳሰብ በማነፅና በመገንባት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል። የጥበብ ሥራዎች የአገርን የጋራ እሴቶች እያጎሉ የህዝቦች መቀራረብና አንድነትን በማጠናከር የማይተካ ሚና እንደሚጫወቱ አያጠራጥርም። በማህበረሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ ስህተቶችን እያረመ በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ በመገንባትም የሚስተካከለው የለም። አንጋፋው የጥበብ ሰው አርቲስት ደበበ እሸቱ እንደሚለው የጥበብ ሰዎች በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመገንባት ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚነሱ ሁከትና ብጥብጦች ህይወት የሚያጠፉና የአገርና የወገን ሀብትና ንብረት የሚያወድሙ ጥቂት አካላት ተስተውለዋል። ይሄን ለማረም የጥበብ ሰዎች በየተሰማሩበት ዘርፍ የተፈጠሩ ስህተቶች እንዳይደገሙ በጥበብ ከሽነው በማቅረብ ትውልዱ ከሰራው ስህተት እንዲማር የማድረግ ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አርቲስት ደበበ ይናገራል። ተዋናይ ይገረም ደጀኔ በበኩሉ ስህተቶችን ለማረም ሰፊ የጥበብ አስተምህሮ ያስፈልጋል፤ ተደማጭ ሰዎች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የመንግስት ባለስልጣናትና የእምነት ተቋማት ከጥበብ ሰዎች ጋር በመስራት ጠንካራ የአገር አንድነትና ህብረት ለመገንባት ይቻላሉ ብለዋል። “ወደ ማህበረሰቡ የሚተላለፉ መልዕክቶች ጥንቃቄ ይፈልጋሉ” የሚለው ተዋናይ ይገረም በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው የግብረ ገብነት ጉድለትን ለማረም “ሁላችንም የየራሳችን ኃላፊነት መወጣት አለብን” ብሏል። ታዋቂው የሙዚቃ ባለሙያ ሰርፀ ፍሬስብሃት እንደሚናገረው የጥበብ ስራዎች በመዝሙራቸው በቲያትራቸው በስዕላቸው በፊልማቸው ማህበረሰብን ይቀርፃሉ። ማንኛውም የጥበብ ሰው “ቁንጅናና ውበት”ን ከማድነቅ ባሻገር የትውልድ ግብረ ገብነትን የሚያንፁ ሥራዎችን በማበርከት ማህበረሰባዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንደለበት ሊገነዘብ ይገባል ብሏል። አንጋፋ የጥበብ ባለሙያዎቹ ኢትዮጵያውያን የጥበብ ባለሙያዎች አገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን በማበርከት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መክረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም