ኀብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በሚመለከት የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ባለመቀበል ክትባቱን መውስድ አለበት

197

ታህሳስ 4/2014/ኢዜአ/ ኀብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በሚመለከት የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ባለመቀበል ክትባቱን መውስድ እንዳለበት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።

ሚኒስትሯ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ “ኮቪድ-19 በኤች አይ ቪ/ ኤድስ የማከም ሂደት ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተጽዕኖ እና በኃይማኖታዊ አስተምህሮ ለመከላከል የኃይማኖት መሪዎች ሚና” በሚል በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነው።

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኮቪድ ወረርሽኝ ከሚያስከትለው ህመም እና ሞት በተጨማሪ በህዝቦች መስተጋብር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ከዚህ ቀደም ወረርሽኙን ለመከላከል በተሰሩ ሥራዎች የኃይማኖት አባቶች ቁልፍ ሚና ማበርከታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ጉዳት መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት ።

የኮቪድ ወረርሽኝ አሁንም የዓለማችን ስጋት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤  ከዚህ አኳያ ወረርሽኙን የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ወረርሽኙን ለመከላከል ከሚሰሩ ሥራዎች መካከል ክትባት አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚሰነዘሩ ፀረ-ክትባት ሐሳቦችና አመለካከቶች መታረም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኃይማኖት አባቶች ኀብረተሰቡን በማስተማር ይህ አመለካከት እንዲስተካከል የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ-ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤  በህብረተሰቡ ውስጥ የተሳሳተ መረጃ የሚሰጡ ግለሰቦች እና ቡድኖችመኖራቸውን ተናግረዋል።

ይህም የወረርሽኙን ሥርጭት የመከላከል ሥራው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸው፤ ድርጊቱ   በኃይማኖት አስተምህሮ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ክትባት መውሰዳቸውን  ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።