"የበቃ"/'Nomore'/ ዓለም አቀፍ ዘመቻ ውጤት እያመጣ ነው- ምሁራን

68

ሚዛን አማን፤ ታህሳስ 5/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የከፈቱት "የበቃ"/'No more'/ ዓለም አቀፍ ዘመቻ ውጤት እያመጣ መሆኑን ምሁራን አስታወቁ።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የህግ ምሁሩ አዳነ ኮርቦ ለኢዜአ እንደገለጹት አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት ኢትዮጵያ ያላትን እውነት እንዳላዩ በማለፍ በሀሰት መረጃዎች በጎ ገጽታዋን እያበላሹ ነው።

የኢትዮጵያን ወድቀት ለፋጠን የምትሰራው አሜሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተረጋገጠውንና  በአሸባሪው ህወሓት የተፈጸመውን የማይካድራን የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል ወደ ጎን በመተው "ትግራይ ጀኖሳይድ" በማለት በኢትዮጵያ ላይ ጥላሸት እየቀባች እንደምትገኝ አመልክተዋል።

ውንጀላዋን ለማጠናከር ምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን የሀሰት ዘገባዎች በማስረጃነት እንደምትጠቀም አብራርተዋል።

በዚህ የተቆጩት በሀገር ውስጥ እና በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያን የከፈቱት የበቃ/Nomore/ እንቅስቃሴ መልካም ነገሮችን ይዞ እየመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ለመወንጀል በአሜሪካ ሲዘጋጅ የነበረው ረቂቅ አዋጅ በሀገሪቱ ብሔራዊ መከላከያ ፍቃድ መታገዱ ለዚሁ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይሄም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ እያራመደች ላለው ያልተገባ ጫና የማሰቢያ ጊዜ የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል።

ዲያስፖራው ባለበት ሁሉ ስለሀገሩ ክብር ዘብ በመቆም ጫና እየፈጠረ መሆኑን የገለጹት ምሁሩ፤ አጋጣሚው አንድነቱን እንዲያጠናክር እድል መስጠቱን አስታውቀዋል።

አሜሪካ በተከፈተው የኢትዮጵያን የበቃ እንቅስቃሴ  ውንጀላዋን የምታቆም ከሆነ የሀሰት መረጃዎች  ጠንሳሽና አቀባይ መገናኛ ብዙሃን ራሳቸውን እንዲመለከቱ እድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለትካል ሳይንስና የታሪክ ምሁር ዶክተር ንጉስ በላይ በበኩላቸው "የውንጀላ ሰነዱን አዘገዩ ማለት አቆሙ ማለት ስለማይሆን የተጠናከረ ሥራ በመስራት ጫና መፍጠሩ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል።

የሀሰት መረጃዎች በኢትዮጵያ ላይ ጫናዎችን ማስከተላቸውን የጠቆሙት ምሁሩ፤ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የጀመሩትን ትግል አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው  ጠቁመዋል።

አሜሪካ በአሸባሪው ህወሓት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የማይካድራ የዘር ጭፍጨፋን በህግ አይን ከማየት ተቆጥባ ያልተጻፈ እያነበበች መሆኗን ጠቁመዋል።

ይሄም ለኢትዮጵያ ያላትን ጭፍን ጥላቻና ያላትን ሀገር የማፍረስና ህዝብ የመበተን ፍላጎት በግልፅ የሚያሳይ መሆኑን  አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን እውነት በልጆቿ ገሃድ አውጥታ እያሳየች የምታሸንፍ እንጂ በጫና ብዛት የምትንበረከክ ሀገር እንዳልሆነች ምሁራኑ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም