ምክር ቤቱ የተለያዩ አዋጆችና ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ

79

ድሬዳዋ፤ ታህሳስ 5 ቀን 2014 (ኢዜአ) የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች ፣ የመንግስት ተጠሪዎችና ዳኞችን ሹመት በማጽደቅ ተጠናቀቀ።

189 መቀመጫዎች ያሉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው  አስቸኳይ ጉባኤ የአስተዳደሩ አስፈጻሚና ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አካላትን እንደገና ለማቋቋም ብሎም ተግባራትና ኃላፊነት ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጅ ፣ የድሬዳዋ የከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት፣ የድሬዳዋ መዋቅራዊ ፕላን ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ሰፊ ውይይት አካሂዷል፡፡

አዋጆቹ ለነዋሪው ህዝብ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡

በአስተዳደሩ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሂደት ውጤታማና ዘላቂ ለማድረግ ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ነው የተመለከተው፡፡

በተለይ የቀጣይ አስር ዓመታት ሁለንተናዊ ዕድገት በአግባቡ ለመምራት ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት የድሬዳዋ ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ወሳኝ አስተዋጽኦ እንዳለው በጉባኤው ላይ ተገልጿል፡፡

የምክር ቤቱ የከተማ ልማት ኮንስትራክሽንና የማዘጋጃ ቤት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አንድነት ሐይሉ የከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን እስካሁን በህግ ያልጸደቀ መሆኑ አበይት የፕላን ጉዳች ላይ ውሳኔ መስጠት ላይ ክፍተት ፈጥሯል ብለዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ለውጡን የተከተለ ዕድገት ለማምጣት የከተማዋን ልማትና ዕድገት ሥርዓት ባለው ሁኔታ መምራት እንዲቻል ስለከተማ ልማትና መዋቅራዊ ፕላን የሚደረግ ህግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት ረቂቅ አዋጆች ለተገልጋዮች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዙ መሆናቸውን ገልጸው፤ አዋጆቹ በከተማ ዙሪያ ያሉ የገጠር ቀበሌዎችን ከግምት ማስገባት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በአዋጆቹ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ አጽድቀዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ፈትሂያ አደን ረቂቅ አዋጆቹ የድሬዳዋ አስተዳደር ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያረጋግጡና የተጠያቂነትን ባህልን ከፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለአዋጆቹ ተግባራዊነት የሚደረገው ድጋፍ ፣ክትትልና ቁጥጥር ይጠናከራል ብለዋል፡፡

የምክር ቤቱ ጉባኤ በተጨማሪም አቶ ሻኪር አህመድ፣ አቶ ደረጃ ፀጋዬና አቶ ገዛኻኝ ታዲዮስ በምክር ቤቱ ረዳት የመንግስት ተጠሪ አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡

እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደር ይገባኝ ሰሚና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስድስት ዳኞችን ሹመት በሙሉ ድምጽ ያፀደቀ ሲሆን የምክር ቤቱን ሰባት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ የሚያገለግሉ የ28 አባላት ሹመትም አጽድቋል፡፡

ተሿሚዎቹም የተጣለባቸውን ህዝባዊና መንግስታዊ ኃላፊነት  ህገ መንግስቱንና ህጎችን መሠረት በማድረግ በታማኝነት እንደሚያገለግሉ ቃል-መሃላ በመፈጸም የምክር ቤቱ አስቸኳይ ጉባኤ መረሃ ግብሩን አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም