መገናኛ ብዙሃን ለህዝቡ መረጃ ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ ለተጎዱ ወገኖችም ድጋፍ በመስጠት ደራሽ ሊሆኑ ይገባል

82

ታህሳስ 5/2014/ኢዜአ/ መገናኛ ብዙሃን ለህዝቡ መረጃ ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ ለተጎዱ ወገኖችም ድጋፍ በመስጠት ደራሽ ሊሆኑ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ዑሙድ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ሰራተኞች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል በዛሬው እለት የአይነት ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ዑሙድ፤ መገናኛ ብዙሃን ለህዝቡ መረጃ ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖችም ድጋፍ በመስጠት ደራሽ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

ኢዜአ ወቅታዊ መረጃዎችን በፍጥነትና በጥራት ተደራሽ በማድረግ እያከናወነ ያለውን የላቀ ሚና ጠቅሰው ሰራተኞቹ ደግሞ ለተፈናቀሉ ወገኖች ባደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

በተለይም ድጋፍ የሚሹ ወገኖች እገዛ እንዲያገኙ  ምቹ መደላድል ለመፍጠርና የሕብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲጎለብት ከመነቃቃት አንፃር በኃላፊነት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በኢዜአ የሴቶችና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክተር ታደለች ቦጋለ፤ የተቋሙ ጋዜጠኞች በተለያዩ አውደ ግንባሮች በመንቀሳቀስ ለሕዝብ ተጨባጭ መረጃ ተደራሽ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አጠቃላይ የኢዜአ ሰራተኞች የወር ደሞዛቸውን ለአገር መከላከያ ሰራዊት በመለገስ አጋርነታቸውን ማሳየታቸውን አስታውሰው በዛሬው እለት ደግሞ ለተፈናቀሉ ወገኖች የአይነት ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

የዛሬው ድጋፍ አልባሳት፣ ጫማ፣ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ፣ ሳሙና እና የምግብ ቁሳቁስ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ሰራተኛው የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢዜአ ሰራተኞች ለሰራዊቱ በየሶስት ወሩ በቋሚነት የደም ልገሳ እያካሔዱ መሆናቸውንም ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም