አካል ጉዳተኞችን የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ክፍተት መኖሩ ተመለከተ

49
ባህር ዳር ነሀሴ 18/2010 አካል ጉዳተኞችን በሁሉም የልማት መስክ ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርግ የህግ ማእቀፍ ቢኖርም በአፈጻጸም ግን ሰፊ ክፍተት መኖሩን አንድ ጥናት አመለከተ። ''የአካል ጉዳተኞች የሚገጥሟቸው ችግሮች፣ የችግሩ ስፋትና ጥልቀትና የመፍትሄ አቅጣጫዎች'' ላይ መሰረት ባደረገው ጥናት ላይ በባህርዳር ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል። በአገር አቀፍ ደረጃ የአይነ ስውራን ማህበራት ጥምረት ፕሬዝዳንት አቶ ጌቱ ሙላቱ ጥናቱን ሲያቀርቡ እንዳሉት በዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት መሰረት በኢትዮጵያ ከሚኖረው ህዝብ 17 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆነው አካል ጉዳተኛ ነው፡፡ እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ መንግስት የአሰሪና ሰራተኛ ና የህንጻ አዋጆች ማውጣቱ  በጎ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የወጡ አዋጆችን በመፈጸም በኩል ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ በትምህርትና ስልጠና፣ የስራ ስምሪትና የኮንስትራክሽን ተቋማት ላይ ያተኮረ ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል፡፡ በጥናቱ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ህጎች የተበታተኑ መሆናቸውና በህገ መንግስቱ አንቀጽ 45 ነጥብ 5 ያለው ድንጋጌ “የመንግስት አቅም በፈቀደ መልኩ” የሚለው ከዓለም ህጎች ተጻራሪ መሆኑ ክፍተት እንደሚፈጠር ተመልክቷል። በተጨማሪም የአስፈጻሚ አካላት የግንዛቤ ማነስ፣ የአካል ጉዳተኞች የዝቅተኝነት ስሜት አለመለወጥ፣ ሚዲያው የአካል ጉዳተኞችን የተመለከተ ዘገባዎችን የአቅዱ አካል አድርጎ ከመስራት ይልቅ ገንዘብ መጠየቅ የሚሉት የጥናቱ ግኝቶች ናቸው። መፍትሄውም እንደ ሴቶችና ህጻናት ፖሊሲ ሁሉ አንድና ወጥ የሆነ የአካል ጉዳተኞች ፖሊሲ ማውጣት፣ በህገ መንግስቱ ያለው የእርዳታ ስዕል ያለውን ድንጋጌ ማሻሻል፣ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መስራት የሚሉት ተቀምጠዋል። በአማራ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ደህንነት ማስፋፊያ ደይሬክተር አቶ በላይነው ጸጋ እንዳሉት ጥናቱ በመላምት ሲነሱ የነበሩ ችግሮችን ያረጋገጠ ነው። የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ለማካተት የወጡ ህጎችና መመሪያዎች የአፈጻጸም  ችግሮችን  ጥናቱ  መለየቱን ተናግረዋል። በመሆኑም ቢሯቸው በጥናቱ ግኝትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በመውሰድ እስካሁን  ያልተገበሩ የአስፈጻሚ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ በየደረጃው ከሚገኙ ምክር ቤቶች ጋር በመተባበር ለመስራት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። የቸሻየር ኢትዮጵያ የባህርዳር ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ መሃመድ ሃሰን በበኩላቸው ድርጅታቸው የአካል ጉዳት ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በትምህርት ቁሳቁስ፣ ዊልቸርና ክራንች ና ሌሎች ድጋፎችን እየተደረገ ይገኛል። በተካሄደው መድረክ የበላይ አመራሮች አለመሳተፋቸው  ጥናቱ ያወጣቸውን ችግሮች በቀጣይ ለመቅረፍ የሚያስችል ሆኖ አልታየኝም ያሉት ደግሞ በባህርዳር ከተማ የአካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን የህዝብ ግንኙነት አቶ ታፈረ አታላይ ናቸው። ለአንድ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክ የአካል ጉዳተኛ ማህበራትና ፌደሬሽን አመራሮች፣ የአስፈጻሚ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም