በምግብ ራሷን የቻለች ሀገር ለመፈጠር ለተፋሰስ ልማትና ጥበቃ ትኩረት ተሰጥቷል

62

አዳማ፣ ታህሳስ 04/2014(ኢዜአ) የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራሷን የቻለች ሀገር ለመፈጠር በተፋሰስ ልማትና ጥበቃ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ግብርና ሚንስቴር አስታወቀ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የዘንድሮው የበጋ ወቅት የተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በአዳማ ተካሂዷል  ።  

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤሊያስ በወቅቱ እንደገለፁት የተፈጥሮ ሀብት ልማት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ለሀገራዊ ሉዓላዊነት መረጋገጥ የላቀ ሚና አለው።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የአፈር መሸርሸር፣ የአፈር አሲዳማነት መጨመር፣ የደን ምንጣሮ፣ የግጦሽ መስፋፋትና ህገወጥ ሰፈራ "ለተፈጥሮ ሀብት መመናመን ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።

"በዚህም ሀገራችን የምግብ ዋስትናዋን ማረጋገጥ ተስኗት ለተመፅዋችነትና ለውጭ እርዳታ ጥገኛ ሆናለች" ብለዋል።

"እርዳታ ሰጭ ሀገራት በድጋፍ ስም እጃችንን እየጠመዘዙ ፍላጎታቸውን ሊጭኑብን ይሻሉ" ያሉት  ፕሮፌሰር ኢያሱ ሁኔታውን ለመቀልበስና ሉዓላዊነታችንን ለማስከበር የተፋሰስ ልማት ላይ በትኩረት መስራት አለብን" ሲሉ በአጽኖት ተናግረዋል።

የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ ህዝቡ አሸባሪውን ህወሃትና ተላላኪዎቹን በግንባር ከመፋለም ጎን ለጎን የሚያከናውነው መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።

የተፋሰስ ልማት ስራው  ከጥር 2014 ዓም  መጀመሪያ እንደሚጀመር ያመላከቱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ህዝቡ በህልውና ዘመቻው እያስመዘገበ ያለውን ድል በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ዘርፍ መድገም እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል ።

ለመጪው ክረምት የሚተከሉ ችግኞችን ማዘጋጀት፣ የአፈርና ውሃ ዕቀባ፣ ባለፈው ክረምት የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ ደግሞ በተፋሰስ ልማትና ጥበቃ ስራ የሚከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ፅሑፍ ያቀረቡት በግብርና ሚንስቴር የተፋሰስ ልማት ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ታደሰ በበኩላቸው የዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ስራ በ5 ሺህ ተፋሰሶች ላይ የሚከናወን መሆኑን አመልክተዋል።

"ከኢትዮጵያ በዓመት ከ2 ቢሊዮን ቶን በላይ አፈር በጎርፍ ተጠርጎ ወደ ውጭ አገራት ይሄዳል" ያሉት ዳይሬክተሩ፤ "ግብጽና ሱዳን በእኛ በሚያገኙት ለም አፈር የሚያለሙትን ስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ መልሰው ይልኩልናል " ሲሉ የችግሩን አንገብጋቢነት ገልጸዋል።

የግብርና ስራችንን ከተፈጥሮ ዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ የሚያስችለንን የተፋሰስ የመስኖ ልማት ስራ በተቀናጀ መልኩ ማከናወን ይገባናል" ሲሉ አስገንዝበዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀን በሚቆየው የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ ላይ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም