ልማት ባንክ አሸባሪው ህወሓት ያደረሰውን ውድመት ለማካካስ የግብርና መሳሪያዎች በሊዝ ለማቅረብ ተዘጋጅቷል

168

ታህሳስ 4/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ወራሪ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ያደረሰውን ውድመት ለማካካስ በቀጣዮቹ የምርት ወቅቶች የግብርና መሳሪያዎች በሊዝ ለማቅረብ የፋይናንስ ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አስታወቀ።

የባንኩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት የሽብር ቡድኑ ባንኩ በሚደግፋቸው ፕሮጀክቶች ላይ ያደረሰውን ተፅዕኖና ውድመት የሚያጠና ቡድን አሰማርቷል።

በርካቶቹ ባንኩ የሚደግፋቸው ፕሮጀክቶች በትግራይ ክልል የሚገኙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የደረሰው ውድመት በባንኩ ጤናማነት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑንም አመላክተዋል።

ከአሸባሪው ወረራ ነፃ በወጡ አካባቢዎች የሚገኙ ፕሮጀክቶችን መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

ባንኩ በአሸባሪ ቡድኑ የደረሰውን ውድመት ለማካካስ በቀጣዮቹ የምርት ወቅቶች የግብርና መሳሪያዎችን በሊዝ ለማቅረብ መዘጋጀቱንም ዶክተር ዮሃንስ አስታውቀዋል።

ባንኩ በርካታ ዘርፎችን ሲደግፍ የነበረና ዕድሜ ጠገብ ቢሆንም የአሸባሪ ቡድኑ አባላት ስልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ ሲከተሉት በነበረው ያልተገባ አካሄድ አሰራሩ ጤናማ ሂደትን ያልተከተለ እንደነበረም ተናግረዋል።

በስርዓቱ ተጠቃሚ የነበሩ ሰዎች ያለ አግባብ ሲደገፉ እንደነበር አስታውሰው አንዳንድ የውጭ ባለሃብቶች ጥቅም ላይ የዋሉ መሳሪያዎች ወደ አገር ውስጥ በማስገባት የባንኩን ሀብት ያለ አግባብ እንዲጠቀሙ ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል።

በወቅቱ ከነበሩ ባለስልጣናት ጋር ቅርበት ያላቸው ሰዎችም የወሰዱትን ብድር ሳይከፍሉ ዓመታት መቆጠራቸውን አስረድተዋል።

ባንኩ ያልተገቡ አሰራሮችን ለማስወገድ ባከናወናቸው የሪፎርም ስራዎች የተበላሸ ብድርን ከነበረበት 35 በመቶ ወደ 26 በመቶ ማውረድ መቻሉን ገልፀዋል።

ባንኩ ለተለያዩ ኢንተርፕራይዞች የፕሮጀክትና ሊዝ ፋይናንሲንግ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑ ተገልጿል።