"ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ሉዓላዊነትና ሕልውና አይደራደሩም" በግሪክ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባላት

82

ታህሳስ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ሉዓላዊነትና ሕልውና እንደማይደራደሩ በግሪክ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባላት ገለጹ።

'የበቃ' ወይም '#NoMore' ሰላማዊ ሰልፍ ትናንት በግሪክ መዲና አቴንስ መነሻውን አቴንስ 'ሲንታግማ ስኩዌር' በማድረግ በግሪክ ፓርላማና አሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት ተካሄዷል።

በግሪክ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባላት በሰልፉ ላይ አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነት በማውገዝ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰባቸውን የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ዶክተር ዘውዱ ሙሉጌታ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሰልፈኞቹ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን መንግስትና የሕዝቡን ፍላጎት ማክበር እንዳለበትና አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች የፈጸማቸውን አሰቃቂ ድርጊቶች እንዲያወግዙ መጠየቃቸውንና ጥሪ ማቅረባቸውን አመልክተዋል።

አንዳንድ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃኖች በኢትዮጵያ ላይ የሚያሰራጯቸውን ሐሰተኛ ዘገባዎችን እንዲያቆሙ መጠየቃቸውንም ተናግረዋል።

'እኛ ኢትዮጵያውያን በአገራችን ሉዓላዊነትና ሕልውና አንደራደርም'፣'ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጎን ነን' የሚሉና ሌሎች 'የበቃ' እንቅስቃሴ መልዕክቶች በሰልፉ ላይ መተላለፋቸውን ነው ዶክተር ዘውዱ ያስረዱት።

በግሪክ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባላት ለኢትዮጵያ ወቅታዊ ጥሪዎችና የልማት ፕሮጀክቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አመልክተዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ኢትዮጵያውያን፣ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣አፍሪካውያን፣የግሪክ ዜጎችና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች መሳተፋቸው ተገልጿል።

በተያያዘ ዜና 'የበቃ' ወይም '#NoMore' ዘመቻ አካል የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ ትናንት በዴንማርክ መዲና ኮፐንሀገን ተካሄዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም