ለህልውና ዘመቻው የህዝቡ ሁለገብ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል

53

ጎንደር፤ታህሳስ 4/2014 (ኢዜአ) ለህልውና ዘመቻው ህብረተሰቡ የሚያደርገው ሁለገብ ተሳትፎ ከመቼውም ግዜ በላይ መጠናከሩን የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አስታወቁ፡፡

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የሀገር ውስጥ በጎ አድራጊ ግለሰቦች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ስንቅና አልባሳት ለፀጥታ ሃይሉ፣ ለተፈናቃይ ወገኖችና ለዘማች ቤተሰቦች ድጋፍ አድርገዋል።

የከተማው ምክትል ከንቲባና የሀብት አሰባሳቢ ግብረ ሃይል ሰብሳቢ አቶ ባዩህ አቡሃይ በድጋፍ ርክክቡ ስነ ስርአት ላይ እንደገለጹት  ህብረተሰቡ ለህልውና ዘመቻው ያልተቆጠበ ድጋፍ እያደረገ ነው።

ህዝቡ ልጁን መርቆ ወደ ግንባር ከመላክ ጀምሮ  በስንቅ ዝግጅትና በጥሬ በገንዘብ እያደረገ ያለው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የህልውና ዘመቻው በድል እንዲጠናቀቅ በቁሳቁስና በገንዘብ ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ወገኖችን በማስተባበር  125 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዝብና ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የአይነት ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።

እየተደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ምክትል ከንቲባው፤ የድጋፍ ማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢንስትራክተር እንዳልክ ፋውንዴሽን ተወካይ አቶ ሃይሉ ቀለመወርቅ በበኩላቸው ድርጅቱ በደባርቅ ግንባር ለሚገኘው የፀጥታ ሃይል ግምቱ 600 ሺህ ብር የሆነ የአይነት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ግምቱ ከ600 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ ቁሳቁሶችን በተወካያቸው በአቶ አማኑኤል ጌታነህ በኩል ለከተማ አስተዳደሩ አስረክበዋል፡፡

በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በታክሲ ሾፌርነት የሚያገለግሉ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው ከ300 ሺህ ብር በላይ በማዋጣት የገዙትን ምግብ ነክ ቁሳቁስ በጎንደር ከተማ ለሚገኙ የዘማች ቤተሰቦች እንዲውል ለግሰዋል፡፡

የህልውና ዘመቻው  በድል እንዲጠናቀቅ ማህበረሰቡ በጥሬ ገንዘብና በአይነት የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተመላክቷል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም