የአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራትን ጫና ለመቋቋም ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር ያስፈልጋል

67

ሶዶ፤ ታህሳስ 04/2014 (ኢዜአ) የአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራትን ጫና ለመቋቋም ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የሶዶ ዩኒቨርስቲ ምሁራን አመለከቱ።

ለአሸባሪው ህወሓት የሚደረጉ ድጋፎች ተላላኪ መንግስት ለመመስረት ታስቦ መሆኑ ተመላክቷል።

በሶዶ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ አስተዳደርና ልማት አመራር ትምህርት ክፍል ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር አሜን ዲያቆን ለኢዜአ እንደገለፁት አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ከአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጋር በቅንጅት እየሰሩ ነው።

በቅንጅት በሚደረገው ዘመቻ ኢትዮጵያን አስመልክቶ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ዘመቻው የሚፈጥረውን ጫና ለመቋቋም ከመቼውም ጊዜ በላይ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

አለም አቀፍ ጫናውን ለመመከት በተለይ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እውነታውንና የሀገርን በጎ ገፅታ በማጉላት ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት  ሀሰተኛ መረጃ በሚያቀብሉ ተላላኪዎች አማካኝነት በሀገር በጎ ገጽታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያደረሰ መሆኑን አመልክተዋል።

ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከርና የሀገር ውስጥ ባንዳዎች ሴራ ማጋለጥ እንደሚገባም  ጠቁመዋል።

በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ማሞ ኢሳያስ በበኩላቸው አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት ሆን ብለው የሀገርን ገጽታ ለማበላሸት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑ ለምዕራባዊያን ሀገራት የተላላኪነት ስራ በመስራት ውለታ የዋለ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁንም ቡድኑን ወደ ስልጣን በመመለስ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ፍላጎት እንዳላቸው  አስረድተዋል።

ለዚህም የመገናኛ ብዙሃንን ተጠቅመው በኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማሳደር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ነጭ በጥቁር የተሸነፈበት የታሪክ ምዕራፍ ከፋች እና ባለቤት መሆኗን የጠቁሙት ምሁሩ፤ የምዕራባዊያንን የእጅ አዙር ቀኝ አገዛዝ የውስጥ አንድታችንን በማጠናከር መመከት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም