አሸባሪው ህወሃት በትምህርት ቤቶች ላይ ያደረሰው ውድመት ኢትዮጵያ ብቁ አገር ተረካቢ ትውልድ እንዳይኖራት የሚደረገው ሴራ አካል ነው

78

ታህሳስ 4/2014/ኢዜአ/ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በትምህርት ቤቶች ላይ ያደረሰው ውድመት ኢትዮጵያ ብቁ አገር ተረካቢ ትውልድ እንዳይኖራት የሚደረገው ሴራ አካል መሆኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አስታወቀ።

ማህበሩ ውድመት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለማልማት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በወረራ ይዟቸው በቆየባቸው አካባቢዎች በዋናነት የህዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ ፈጽሟል፡፡

የሽብር ቡድኑ ውድመት ካደረሰባቸው ተቋማት መካከል ደግሞ የነገ አገር ተረካቢ ህጻናትን የሚያፈሩ ትምህርት ቤቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ በንቲ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የትምህርት ቤት ታዳጊዎች ቀጣይ የህይወት ጉዟቸውን የሚለዩበት፣የሚታነጹበትና በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር እንዲበቁ የሚታገዙበት እንጂ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ ተቋም አይደለም።

ትምህርት ቤት በጦርነት ወቅት ከማይነኩ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ነገር ግን አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የትምህርት ተቋማትን ከማውደም ባሻገር በርካታ የትምህርት መገልገያ ቁሳቁሶችን መዝረፉን ጠቅሰው፤ ይህም የአሸባሪ ቡድኑን የአስተሳሰብ ዝቅጠት እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በትምህርት ቤቶች ላይ ያደረሰው ውድመት ኢትዮጵያ ብቁ አገር ተረካቢ ትውልድ እንዳይኖራት የሚደረገው ሴራ አካል መሆኑንም የማህበሩ ፕሬዝዳንት አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም አሸባሪ ቡድኑ በትምህርት ተቋማት ላይ ያደረሰውን ውድመት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በግልጽ ሊያወግዘው ይገባል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ማህበሩ ውድመት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት መልሶ ለማልማት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ በቅርቡ በአማራ ክልል የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የ50 ሺህ ብር ደጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ በቀጣይም በተመሳሳይ ለአፋር ክልል ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል፡፡

ድጋፉም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዩሃንስ በንቲ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም