የደን ልማትን በአግባቡ መምራት ባለመቻሉ ከዘረፉ የሚገባው ምጣኔ ኃብታዊ ጥቅም እየተገኘ አይደለም

56
አዲስ አበባ ነሃሴ 18/2010 በኢትዮጵያ የደን ልማትን በአግባቡ መምራት ባለመቻሉ አገሪቱ ከዘረፉ ማግኘት የሚገባትን ምጣኔ ኃብታዊና ስነ-ምህዳራዊ ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ የዘረፉ ባለሙያዎች ገለፁ። የኢትዮጵያ ፎረስተሪ ሶሳይቲ በኢትዮጵያ የደን አሳሳቢ ችግሮችና የወደፊት አቅጣጫ ላይ ያዘጋጀው ውይይት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሄዷል። በዚሁ ወቅት እንደተገለፀው ኢትዮጵያ ቡናና ሰሊጥን የመሳሰሉ የሰብል ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ጣውላን ጨምሮ ከውጭ አገር ለምታስገባቸው የተለያዩ የደን ውጤቶች ከምታወጣው የገንዘብ መጠን ጋር ተቀራራቢ ነው። ይህም አገሪቱ ደንን በተጠና መንገድ በማልማት ለምጣኔ ኃብታዊ ጥቅም ማዋል እንዳልቻለች ያሳያል ተብሏል። የዘረፉ ልማት ደካማ መሆን ከምጣኔ ኃብታዊ ኪሳራ ባሻገር አገሪቱ በውሃ እጥረት፣ በአፈር መሸርሸርና በጎርፍ አደጋዎች እንድትጠቃ እያደረጋት መሆኑም ተመልክቷል። የደን ልማትንና ጥበቃን እንዲከታተል የተቋቋመው መንግስታዊ ተቋም አደረጃጀት ለተደጋጋሚ ጊዜያት መቀያየር እና ለተለያዩ መስሪያ ቤቶች ተጠሪ መደረጉ ዘረፉ በአግባቡ አንዳያድግ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል መሆኑም በዚሁ ወቅት ተመልክቷል። የሶሳይቲው ፀሀፊ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ እንደተናገሩት የደን ልማት ኃብትን በማጠናከር ለምጣኔ ኃብታዊና ስነ-ምህዳራዊ ጥቅም ማዋል ይቻል ዘንድ በዘርፉ የሚደራጁ ተቋማት እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ዘልቀው የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። የዘርፉን ተቋማት በተጠና መልኩ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ በማደራጀት ዘርፉን ማልማት ከተቻለ አገሪቱ እንጨትና የእንጨት ውጤቶችን ከሌሎች አገሮች ለማስገባት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን ይቻላል ሲሉ ነው ዶክተር አደፍርስ የተናገሩት። ኢትዮጵያ ለደን ልማት የተመቸ መልክዓ ምድር ያላት አገር መሆኗን የጠቀሱት ዶክተር አደፍርስ፤ ዘርፉ በእውቀትና በትክክለኛ መዋቅር ከተመራ ከአገር ፍጆታ ባሻገር ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የደን ውጤትን የማምረት አቅም መፍጠር እንደሚቻልም ገልፀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም