የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ባለፉት አምስት ወራት 9 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ የፋይናንስ ወንጀሎችን ለህግ አካላት አስተላልፏል

414

ታህሳስ 3/2014/ኢዜአ/ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ባለፉት አምስት ወራት 9 ቢሊዮን ብር በሚገመቱ የፋይናንስ ወንጀሎች ላይ ትንተና አድርጎ ለህግ አካላት ማስተላለፉን አስታወቀ።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች ካደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ባሻገር የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮችን እየፈፀመ መሆኑ ይታወቃል።

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎትም ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት ህገ-ወጥ የሆኑ የውጭና የአገር ውስጥ የገንዘብ ዝውውሮችን እንዲያዙ እያደረገ ይገኛል።

ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመተባበር ባካሄደው ጠንካራ ምርመራ ወደ አሸባሪው ቡድን ሊገባ የነበረ ከ276 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲቀር ማስደረጉ ይታወሳል፡፡

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ  እንዳለ አሰፋ፤ ባለፉት አምስት ወራት  ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ሀብትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮች በተመለከተ አገልግሎቱ መረጃዎች ሲያሰባስብ መቆየቱን ጠቁመዋል።  

በተገኙ ጥቆማዎች መሰረት በርካታ መረጃዎች ተተንትነው ለህግ አስከባሪ አካላት መተላለፋቸውንም ገልፀዋል።

በጥቆማዎቹ መሰረትም የተለያዩ ወንጀሎችን ሲፈፅሙ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ ሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ ባለፉት አምስት ወራት 9 ቢሊዮን ብር በሚገመቱ የፋይናንስ ወንጀሎች ላይ ትንተና አድርጎ ለህግ አካላት አስተላልፏል ብለዋል።

በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መረጃዎችን ማሰባሰብ፣ መተንተንና ከማሰራጨት በተጨማሪ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል በስሩ በርካታ የኢኮኖሚ አሻጥሮች እንዳሉት አብራርተው ወንጀሉ በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑንም ተናግረዋል።

በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ፣ የታክስ ጥሰት፣ ህገ-ወጥ ሐዋላ፣ ገንዘብ አስመስሎ መስራት፣ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ ከ20 በላይ ወንጀሎችን የሚያጠቃልል መሆኑን በመጠቆም።

ከወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የውጭ አገር ዜጎች ጭምር የተሳተፉበት የኢትዮጵያንና የተለያዩ አገራት ገንዘብን አስመስሎ መስራት ወንጀሎች ቢበራከቱም በህዝብ ጥቆማ በቁጥጥር ሰር እየዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህን ወንጀሎች በቅንጅት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር የመግባቢያ ስምምነቶች በመፈረም እየተሰራ ሲሆን ተጠናክሮም የቀጥላል ብለዋል።

ወንጀሎቹ ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸው ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር ጥምረት በመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል

አገልግሎቱ ተቋማዊ አቅሙን ለማጠናከር የቴክኖሎጂ አሰራሮችንና የሰው ሃይሉን የማጎልበት ስራ እየሰራ መሆኑንም አቶ  እንዳለ ጠቅሰዋል።

ህብረተሰቡ ማንኛውም ኢኮኖሚያዊ ወንጀሎች ጋር የተያያዘ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለፋይናንስ መረጃ አገልግሎት በአካልም ሆነ በስልክ ጥቆማ እንዲያደርስም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም