አሸባሪው ህወሓት የትምህርት ተቋማትን በማውደም የክፋት ጥጉን አሳይቷል --ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

104

ባህር ዳር ፤ታህሳስ 3/2014(ኢዜአ)አሸባሪው ህወሓት በትምህርት ተቋማት ላይ በፈፀመው ውድመት የክፋት ጥጉን አሳይቷል ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ ።

ሚኒስትሩ ከትምህርት ሚኒስቴርና ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከፍተኛ አመራሮች ጋር አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ወሎ ዞን ካወደማቸው መካከል የኮኪት ሁለተኛ ደረጃንና የደብረዘቢጥ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ተመልክተዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ በወቅቱ እንዳሉት፤ አሸባው ቡድን ያደረሰው ጥፋት የውጭ ወራሪ ቢመጣ ከዚህ የባሰ ጉዳት ሊያደርስ ከሚችለው በላይ ነው።

በዚህም አሸባሪው ቡድን ለዘረፋ ብቻ እንዳልመጣ ድርጊቱ እንደሚያሳይ አስረድተዋል።

''በእነሱ እምነት ትምህርት ቤቶቹ ተመልሰው የመማር ማስተማር አገልግሎት እንዳይሰጡ ማፈራረስና ማውደም ነው፤ የእኛ ሥራ የሚሆነው ትምህርት ቤቶችን ከዚህ ቀደም ከነበሩበት በተሻለ ሁኔታ መልሶ መገንባት ነው''ብለዋል።

ትምህርት ቤቶቹ ደረጃቸውን ጠብቆ ለመገንባት የባለድርሻ አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

አሸባሪው ህወሓት በትምህርት ቤቶቹ ላይ አስከፊ ውድመት በመፈፀም በትክክል ከወራሪ የሚጠበቅ ተግባሩን አስመስክሯል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ማተቤ ታፈረ ናቸው።

በክልሉ ከ4 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉና በከፊል መውደማቸውን ጠቁመው፤እነዚህን የትምህርት ተቋማት መልሶ በመገንባት ተማሪዎችን ወደ መማር ማስተማር ሂደት ለመመለስ  ይሰራል ብለዋል።

''ትምህርት ቤቶችን ወደ ሜዳነት ቀይሯቸዋል'' ያሉት ሃላፊው፣የትምህርት ተቋማትን ከማውደሙም በላይ ከኢትዮጵያዊነት ባህል ያፈነገጠ አስነዋሪ ተግባር መፈፀሙን አስረድተዋል።

አሸባሪው ህወሃት በትምህርት ቤቶች ግቢና መማሪያ ክፍሎችን ሳይቀር የጅምላ መቃብሮች በማድረግ  በትውልዱ ውስጥ መጥፎ ታሪክ ጥሎ እንደሄደም ገልጸዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን  ምክትል አስተዳዳሪና ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጋሻው አስማሜ  በበኩላቸው፤ በዞኑ ካሉ 912 የትምህርት ተቋማት ሁሉም ላይ ጥቃትና ውድመት መድረሱን አስታውቀዋል።

ቡድኑ በኢትዮጵያ ቀርቶ በዓለም ላይ ተደርጎ የማይታወቅ ዘግናኝ ግፍ መፈጸሙን ጠቅሰው፤ የቡድኑ ዋና ዓላማ በትውልድ ላይ ዘላቂ ጥቃት ማድረስና ማሸማቀቅ ነው ብለዋል።

በዚህም ሀገር ተረካቢ ትውልድ የሚያፈሩ ትምህርት ቤቶችን በማውደም ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ አመልክተዋል።

ትምህርት ቤቶችን መልሶ መገንባትና ማቋቋም ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ተባብረው ትምህርት ቤቶቹ ከነበሩበት ደረጃ በተሻለ እንገነባቸዋለን  ነው ያሉት።

ሚኒስትሩ በስፍራው በነበራቸው ቆይታ፤ ትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ የጅምላ መቃብሮች ፣ ከጥቅም ውጭ የሆኑ መማሪያ መጻህፍት፣ ወንበሮችንና ጠረጴዛዎችን ተመልክተዋል።

ኮምፒዩተሮች፣ ፕላዝማ ቴሌቭዥኖች፣ ቤተ ሙከራዎችንና ሌሎች ለመማር ማስተማር የሚያግዙ ቁሳቁስን እንዳወደመም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም