በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኘው ኢትውድ የተባለ የቻይና ኩባንያ ማሽነሪ በአሸባሪው ህወሃት ቡድን ሙሉ በሙሉ ተዘርፏል

286

ታህሳስ 3/2014 (ኢዜአ)በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኘው ኢትውድ የተባለ የቻይና ኩባንያ ማሽነሪና ግብአቱ በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ሙሉ በሙሉ ተዘርፏል።

አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ በመነሳት በተለይም በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች በህዝብ፣ በመንግስትና በግለሰብ ንብረቶች ላይ ዘረፋና ውድመት ፈፅሟል።

አሸባሪው ቡድን የህዝብ መገልገያዎችን፣ መሰረተ ልማቶችን፣ ኢንዱስትሪዎችን እንዲሁም የግል ድርጅቶችና የመኖሪያ ቤቶችን ጭምር በመዝረፍ በየደረሰባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ውድመት አድርሷል።

አሸባሪው ህወሃት ዘረፋና ውድመት ከፈፀመባቸው አካባቢዎች መካከል በኢንዱስትሪ ከተማነቷ የምትታወቀው ኮምቦልቻ ትጠቀሳለች።

በአካባቢው የደረሰውን ውድመት ለመመልከት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት የተውጣጣ ቡድን ጋር በመሆን በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የደረሰውን ጉዳት ምልከታ ጀምሯል።

በምልከታውም በኢንዱስትሪ ፓርኩ በ239 ሚሊዮን ብር የተቋቋመውን የቻይና የችቡድ ማምረቻ ፋብሪካ አሸባሪው ሃይል ሰብሮ በመግባት ማሽኖችን ሙሉ በሙሉ መዝረፉንና ማውደሙን አረጋግጧል።

የሚኒስቴሩ የኬሚካልና ግብዓት ኢንዱሰትሪዎች ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መሀመድ ጠይብ፤ ከ300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ይሰራ የነበረው ኩባንያ ሙሉ በሙሉ ዘረፋና ወድመት ተፈፅሞበታል ብለዋል።

ኩባንያው ስራ ከጀመረ አንድ ዓመት የሆነው ሲሆን ኤም ዲ ኤፍ እና ሃርድ ቦርድ የተሰኙ የእንጨት ውጤቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀምሮ ነበር።

አሁን ላይ ግን የኩባንያው ንብረትና ማሽነሪዎች በአሸባሪው ህወሃት ሙሉ ለሙሉ መዘረፋቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።

የጨርቃጭርቅ ምርት ላይ የተሰማራው ሁዋክሱ ሃላፊነቱ የተወሰነ የቻይና የግል ኩባንያ ማሽነሪዎችና የተለያዩ ግብዓቶችም በአሸባሪው ቡድን ተመሳሳይ ዘረፋና ውድመት ተፈፅሞበታል።

ኩባንያው ግምቱ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የንብረት ዘረፋና ውድመት የደረሰበት መሆኑንም ከፋብሪካው የስራ ኃላፊዎች ተገልጿል።

አሸባሪው ህወሃት በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ሁሉ ከህዝብ መገልገያዎች በተጨማሪ ትላልቅ መሰረተ ልማቶችንና በኢትዮጵያ ሙአለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ የውጭ ኩባንያዎችን ጭምር ዘርፏል፤ ያቃተውንም አውድሟል።

አሸባሪ ቡድኑ በብዙ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የሚገኙ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን የሚዘርፈውና የሚያወድመው ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች ጋር ያላት የኢኮኖሚ ትብብርና ትስስር እንዲሰናከልና ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም እንድታጣ ለማድረግ ነው።