በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የሕልውና አደጋ መክቶ አሸናፊ ለመሆን የሁላችንም ተሳትፎ ወሳኝ ነው

45

ታህሳስ 03/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የሕልውና አደጋ በመመከት በአሸናፊነት ለመወጣት የሁላችንንም ተሳትፎ ማጠናከር አለብን ሲሉ የኮሪያ ዘማቾች ቤተሰብ ማህበር አባላት ገለጹ።

ከ200 በላይ የኮሪያ ዘማች ልጆችና የልጅ ልጆች ''ደማችን ለመከላከያ ሰራዊታችን'' በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለተኛ ጊዜ ደም ለግሰዋል።

የማህበሩ መስራች አቶ መስፍን ተክሉ "አያቶቻችንና አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩልንን አገር ለማስቀጠል ሁሉም ዜጋ አቅሙ በፈቀደው ሁሉ በንቃት መሳተፍ አለበት" ብለዋል።

"በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ በመመከት በአሸናፊነት ለመወጣት የሁላችንንም ተሳትፎ የሚጠይቅበት ወቅት ላይ እንገኛለን" ሲሉ ተናግረዋል።

በሕልውና ዘመቻው ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው ''ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ" ብሎ የተነሳን አሸባሪ ሃይል በጋራ በመመከት ክብሯን የጠበቀች አገር ለትውልድ ማሻገር ይገባናልም" ብለዋል።

"ከኢትዮጵያ አልፈው አባቶቻችን የሌሎችን በደል መሸከም አቅቷቸው በመዝመትና ሰላም በማስከበር ያሳዩንን ጀግንነት እያስታወስን እኛ አገራችንን ልናስደፍር አይገባም" ያሉት ደግሞ ከዘማች ልጆች መካከል ወይዘሮ መሰለች ማንጉዳይ ናቸው።

"ለአገሬ አይደለም ደሜን ህይወቴን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ'' ሲሉም አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለይ ወጣቶች አገራቸውን በመጠበቅ፣ የልማት አጀንዳ አንግበው ለስራ መነሳሳትና ለሌሎችም ስራ ፈጣሪ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም