የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የጥሬ ገንዘብና የአይነት ድጋፍ አሰባሰበ

69

ጋምቤላ፤ ታህሳስ 03/2014 (ኢዜአ)፡የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ማህበረሰቡን በማስተባበር በአማራና በአፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማሰባሰቡን አስታወቀ።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የተፈናቀሉ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት በሚችለው ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ  መሆኑን ገልጿል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙሴ ጋጀት ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየውን የድጋፍ ማሰባሰብ መረሃ ግብር አስመልክተው ትናንት ለኢዜአ እንደገለጹት እንደ ሀገር የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ለመሰብሰብ ሲባል ለአንድ ሳምንት ትምህርት እንዲዘጋ መደረጉን አስታውሰዋል።

በጋምቤላ ትምህርት ቤቶች ሳይዘጉ በአማራና በአፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች የትምህርት ማህበረሰቡን በማስተባበር ድጋፍ መሰባሰቡን ተናግረዋል።

ለአንድ ሳምንት በተካሄደው የድጋፍ ማሰባሰቢያ መረሃ ግብር ከተማሪዎች፣ ከመምህራን ፣ከትምህርት ባለሙያዎችና አመራሮች በጥሬ ገንዘብና በዓይነት  2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።

"ከተሰበሰበው ድጋፍ መካከል ከ2 ሚሊዮን ብር የሚበልጠው የጥሬ ገንዘብ ሲሆን ቀሪው በዓይነት የተለገሰ  ነው" ብለዋል።

በዓይነት ከተለገሱት መካከል የምግብ ፍጆታዎች፣ የንጽህና መጠበቂያና የተለያዩ አልባሳት እንደሚገኙበት ጠቁመው ድጋፉ በክልሉ መንግስት አማካኝነት ለተጎጂዎች እንደሚደርስ ጠቁመዋል።

በክልሎቹ የሽብር ቡድኑ በቆየባቸው አካባቢዎች በተለይም በትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ መንግስት በሚሰጣቸው መረጃዎች መገንዘባቸው የገለጹት ኃላፊው "ቢሮው ዘርፉን ለመደገፍ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል" ብለዋል ።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አንዷለም ተስፋዬ ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ጾታ ሃላፊ ወይዘሮ ሰንዳይ ኡቦንግ በበኩላቸው በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች አሜሪካና አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነትና የውጭ መገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጩትን የሀሰተኛ መረጃ በቃ/Nomore/ በማለት  ድምፃቸውን አሰምተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም