የድሬዳዋ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና መምህራን የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ሰበሰቡ

44

ድሬዳዋ ታኅሣሥ 3/2014(ኢዜአ)የድሬዳዋ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና መምህራን የአገር ህልውናን ለማረጋገጥ የዘመቱ ቤተሰቦችን የደረሱ ሰብሎች ሰበሰቡ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ የኢትዮጵያን ህልውና ለማረጋገጥ የተጀመሩ ድሎች በሁሉም መስኮች እንደሚጠናከሩ ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎቹና መምህራኑ በአስተዳደሩ ገጠር  ቀበሌዎች በመዝመት የደረሰ ማሽላና በቆሎ ሰብስበዋል፡፡

በሰብል ስብሰባ ላይ የተሰማራው ተማሪ ሐሰን አለኔ በሰጠው አስተያየት "አገርን ለማዳን የዘመቱ ቤተሰቦችንና የአካባቢያችንን ፀጥታ የሚጠብቁ ሚሊሻዎችን ቤተሰቦችና ልጆች በማገዛችን የህሊና ደስታ ሰጥቶናል" ብሏል፡፡

ትምህርት የሚኖረው አገርና ሰላም ሲረጋገጥ በመሆኑ የአገር ህልውናን ለመጠበቅ የዘመቱ ቤተሰቦችን  መደገፍ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

''ዘማቾቹ አባወራዎች በድል እስኪመለሱ ህጻናት ልጆቻቸውን በትምህርት ማገዝ እፈልጋለሁ'' ብሏል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትንና በድል እየደመቀ የሚገኘው የህልውና ዘመቻ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለዘማቾች ቤተሰቦች አስፈላጊው ድጋፍና ክብካቤ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡

"በከተማና በገጠር ለሚገኙ የዘማች ቤተሰቦች  ይህን መሰል ተግባራት ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል" ብለዋል፡፡

 በተለይ ወጣቶች የዘማች ቤተሰቦችን መደገፍና በመንከባከብ የደጀንነት ተግባራቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡

በግንባር እየደመቀ የሚገኘው ድል በደጀን ድጋፍ፣ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በመጠበቅ፣ ልማትና የህዝብን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ትርጉም ባለው መንገድ ለመመለስ  እየተሰራ መሆኑን ከንቲባ ከድር  ተናግረዋል፡፡

ሰብል ከተሰበሰበላቸው ቤተሰቦች መካከል ልጃቸውን ወደ ግንባር የላኩት ወይዘሮ ኑሪያ አህመድ በበኩላቸው "ሰብላቸውን በመሰበሰብ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፣ አገር የገጠማትን ችግር ለማሻገር በጋራ ለመስራት አንድነታችንን  ማጠናከር ይገባናል" ብለዋል፡፡

''ልጄን ወደ ግንባር አገር ለማዳን መላኬ ያኮራኛል ፤የቀረኝንም አንድ ልጅ ካስፈለገ እልካለሁ''ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም