ተፈናቃይ ወገኖችንና ተቋማትን ለማቋቋም ጠንካራ ርብርብ ያስፈልጋል

61

ደብረ ብርሃን ፤ ታህሳስ 3/2014(ኢዜአን በአሸባሪው የህወሃት ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖችንና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የሁሉም አካላት ጠንካራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

ለተፈናቃይ ወገኖች፣ ለሰራዊቱና ጉዳት ለደረሰባቸው ተቋማት ድጋፍ የሚውል የተለያዩ ተቋማት ከ29  ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሶች አበርክተዋል።

በዚህ ወቅት ሚኒስትሯ  እንዳሉት፤ አሸባሪው ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች በንፁሃን ዜጎች ላይ በታሪክ ሲነገር የሚኖር አሳዛኝ ጭፍጨፋና መፈናቀል አድርሷል።

እንዲሁም ዜጎች የሚገለገሉባቸውና ከፍተኛ መዋለ ንዋይ የፈሰሰባቸው የመንግስት ተቋማት፣ የግለሰቦች ንብረትን ዘርፏል፤ አውድሟል ብለዋል።

ቡድን ያፈናቀላቸውን ወገኖችና የመንግስት ተቋምትን መልሶ በማቋቋም በሚደረገው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ያልተቋረጠ ድጋፍና ርብርብ  ወሳኝ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

የወደሙ ተቋማትን መልሶ ከማደራጀት ጎን ለጎንም ለወጣቶችና ለሴቶች የስራ እድል ፈጠራ ትኩረት መሰጠቱንም ጠቁመዋል።

ሚኒስትሯ ከአራት ተጠሪ ተቋማትና የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አገናኝ ኤጀንሲዎች አሰሪ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የተሰበሰበውን 25 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አስረክበዋል።

ከድጋፉ መካከል 30 ኩንታል በሶ ዱቄት፣ 100 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ 500 የመኝታ ምንጣፍ፣  የእርድ እንስሳት እንዲሁም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ይገኙበታል።

የተደረገውም ድጋፍ ቀጣይነት እንደሚኖረው ጠቅሰው፤ በድጋፉ ለተሳተፉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የፌደራል የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ በበኩላቸው፤ ከሃዲውና አሸባሪው ቡድን  በጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አውስተዋል።

ቡድኑ በገባባቸው አካባቢዎች የወደሙ የህዝብ መገልገያ ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ የሁሉም ትብብር ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም በሀገር ውስጥ መድሃኒትና ምግብ ነክ አምራች ማህበራትን መድሃኒትና መድሃኒት ነክ አስመጭ ድርጅቶችን በማስተባበር 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ቁሳቁስ ድጋፍ መመቻቸቱን ገልጸዋል።

ድጋፉም ለመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ ለጤና ተቋማትና ለተፈናቃይ ወገኖች  የሚውሉ አልባሳት፣ መድሃኒት፣ ምግብ ነክ ቁሳቁሶች፣ የህክምና ቁሳቁስ መሆኑን ጠቅሰው፤ ድጋፉም ተጠናከሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በተመሳሳይ ''ዳያስፓራው ለወገኑ'' በሚል መሪ ሃሳብ ሃና ፋውንዴሽን የግል ድርጅት በማህበራዊ ትስስር ፈንድ ያሰባሰበውን 741 ሺህ 665 ብር ግምት ያለው አንድ ሺህ 402 ብርድ ልብስ ለተጎጂዎች እንዲደርስ ለሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር አስረክቧል።

በአዲስ አበባ የማህበራዊ ትስስር ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ እናት ዓለም መለሰ እንዳሉት፤ ድጋፉ በተለያዩ የውጭ ሃገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተገኘ ነው።

በዚህ አስቸሪ ወቅት ከተቆርቋሪ ወገኖች የተገኘውድጋፍ በቀጥታ ለተጎጂዎች ይከፋፈላል ያሉት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ወልደ አማኑኤል ናቸው።

በተለይ የጤና ተቋማትን ለማደራጀት የሚጠቅሙ ድጋፎች መገኘታቸው ተቋማቱ ፈጥኖው አገልግሎት እንዲሰጡ ያግዛል ብለዋል።

ለተደረገው ድጋፍም ያመሰገኑት አቶ ሲሳይ፤  ነፃ በወጡ አካባቢዎች የሚኖሩ ተፈናቃይ ወገኖች ወደ ቄያቸው እየተመለሱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም