የቻይና አፍሪካ የንግድ ትብብር ለአፍሪካዊያን የገበያ አማራጭን በማስፋት ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው

82

ታህሳስ 3/2014/ኢዜአ/ በየጊዜው እያደገ የመጣው የቻይና አፍሪካ የንግድ ትብብር ለአፍሪካዊያን የገበያ አማራጭን በማስፋት ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የኢኮኖሚ ምሁሩ ክቡር ገና ተናገሩ።

አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም አገራት ከአፍሪካ ጋር ያላቸው የንግድ ግንኙነት የራሳቸውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት ብቻ ባስጠበቀ መልኩ እንዲቀጥል ይሻሉ።

ለዘመናት የዘለቀው ይህ እሳቤያቸው በተለይም በማደግ ላይ ላሉት የአፍሪካ አገራት የእድገታቸው ማነቆ ሲሆን ይስተዋላል።

የአህጉሪቱን ሰፊ የተፈጥሮ ሃብትና የሰው ሃይል እነርሱ በሚፈልጉት መልኩ ብቻ አልምተው ለመጠቀም ስለሚሹ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይገባል።

የንግድ ትስስሮቻቸውን በይበልጥ ወደ ቻይና፣ ህንድና መካከለኛው ምስራቅ ያደረጉ የአፍሪካ አገራት ግን የተሻለ ጥቅም ሲያስገኝላቸው ይስተዋላል።

በተለይም ቻይና በዓለም የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት በመሆኗ ከአፍሪካ አገራት ጋር እየተጠናከረ የመጣው የንግድ ትብብር የሁለትዮሽ ጥቅሙም እያደገ መጥቷል።

የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤቶች ዋና አስተዳዳሪ ክቡር ገና እንደሚሉትም ቻይና በስፋት በአፍሪካ ሀገራት ላይ የጀመረችው የንግድ ትስስር ለአህጉሪቷ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው።

በተለይም የቻይና መንግስት ከአፍሪካ ጋር ለመጀመር ያሰበው የግብርና ምርቶችን ከቀረጥ ነፃ ወደ ቻይና የማስገባት /ግሪን ሌን/ የቻይና- አፍሪካን ትብብርና ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።

ቻይና በአፍሪካ ያላት የንግድ ግንኙነት መርህ ሁሉንም ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል መሆኑንም አብራርተዋል።

በየጊዜው እያደገ የመጣው የቻይና አፍሪካ የንግድ ትብብር ለአፍሪካዊያን የገበያ አማራጭን በማስፋት ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደረግ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከቻይና ጋር  እየተካሔደ ያለውን  የአፍሪካ የንግድ ትብብር በበጎ የማይመለከቱት አንዳንድ የምእራቡ ዓለም አገራት መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

እነዚህ አገራት የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ለማስኬድ በአፍሪካ ላይ ያላቸውን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እሳቤ በመተው ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም