የህግ የበላይነት እንዲከበር የህዝቡና የባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ ነው ተባለ

181
አዲስ አበባ ነሀሴ 18/2010 በኢትዮጵያ የዜጎችን የፍትህ ጥያቄ በመመለስ የህግ የበላይነት እንዲከበር ህዝቡና ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት እንዳለባቸው የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገለፀ። ጠቅላይ ዓቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ እንዳሉት መንግስት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ለማጠናከር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል። መንግስትንና ህዝብን በእጅጉ እያሳሰበ ያለው የዚህ ተግባር ዋና መንስኤዎች የህግ የበላይነትን አለማክበር፣  የዴሞክራሲ ባህል አለመዳበር እና የማህበረሰቡ ግንዛቤ እጥረት መሆናቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ተናግረዋል። በመሆኑም የዜጎች የፍትህ ፍላጎትና ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ የሰዎች ሕይወትና ንብረት ደህንነት እንዲጠበቅና የአገር ሰላም እንዲጠናከር ህዝቡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት የሚሰራበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል ብለዋል። የህግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ የአንድ አካል ስራ ብቻ ባለመሆኑ ተጠሪ ተቋማትን ጨምሮ የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የተለያዩ አካላት፣ የክልል ፍትህ ቢሮዎች፣ የፀጥታ አካላት ከህዝብ ጋር በቅንጅት እንዲሰሩም አቶ ብርሃኑ ጠይቀዋል። ቅንጅታዊ አሰራሩ በፍትህ ስርዓቱ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ፣፣ የተልእኮ ወጥነት እንዲኖርና የሕግና የፍትህ ስርዓት ማሻሻያው ውጤታማና ቀልጣፋ እንዲሆን ያስችላል ነው ያሉት። ህዝቡ መንግስት የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ግዴታ እንዳለበት በማወቅ መብቶቹን ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ማጣጣም እንዳለበት ገልጸዋል። በቅርቡ ሰብዓዊ መብቶችን የሚገድቡና የሚጥሱ ናቸው ተብለው ቅሬታ የሚነሳባቸውን ህጎች የማሻሻል ስራ ተጀምሯል። ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ከተለዩት መካከል የፀረ-ሽብር፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት፣ የመረጃ ነፃነትና የፕሬስ እንዲሁም የመሬት አዋጆች ይጠቀሳሉ።                              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም