የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራትን ጫና ለመመከት ተማሪዎች የድርሻቸውን ይወጣሉ

54

ሶዶ፤ ታህሳስ 03/2014 (ኢዜአ)፡ አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና የማህበራዊ ትስስር ገፆችን በመጠቀም ለመመከት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ።

የሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከ6 ሺህ 700 በላይ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ የ2014 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራ ጀምሯል።

በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት ተወካይ ተማሪ ዳግም አክሊሉ ለኢዜአ እንደገለጸው አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት መገናኛ ብዙሃኖቻቸውን በመጠቀም ኢትዮጵያን የማፍረስ ዘመቻ እያካሄዱ ነው።

የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታና እውነታ ለማንፀባረቅ የተጀመሩ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ዘመቻን በመቀላቀል በሀገር የማዳን ዘመቻው የድርሻውን እንደሚያበረክት ተናግሯል።

መገናኛ ብዙሃን ለበጎ ስራም ሆነ ለእኩይ ተግባር ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ጫና ማሳያ መሆኑን ጠቁሞ፤ ሁሉም አካል ባለው እውቀት የሀገርን ገፅታ ለመገንባት መስራት እንዳለበት ጠቁሟል።

በዩኒቨርስቲው የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ የሆነችው ሰኒያ መሐመድ በበኩሏ የህልውና ዘመቻው ግንባር ላይ በመሄድ ብቻ ባለመሆኑ የማህበራዊ የትስስር ገጾችን በመጠቀም የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ ለመገንባት እንደምትሰራ ገልጻለች።

በየጊዜው ኢትዮጵያን አስመልክቶ የሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎችን በመከታተል የማጋለጥና ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንደምታከናውን ጠቁማለች።

የሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ አሸባሪው ህወሓት የሀገርንና የህዝብን ውለታ በመካድ ሀገር ለማፍረስ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የአሸባሪው ህወሓት ሀገር የማፍረስ ሴራ እየተጋለጠና ኢትዮጵያ የያዘችው እውነት እያሸነፈ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሓት እኩይ ተግባሩን ወደ ህብረተሰቡ ለማስረፅ በትምህርት ተቋማት ሲጠቀም እንደነበር አስታውሰው ይህ እንዳይሆን ዩኒቨርሲቲው ጠያቂና ሀገር ወዳድ ዜጋ ለማፍራት ተግቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ለሴራው መጠቀሚያ መሆን እንደሌለባቸው የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ችግሮች ሲያጋጥሙም የማጋለጥ ስራ መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የመማር ማስተማር ስራው ያለምንም ችግር እንዲከናወን የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም