በአሸባሪው ህወሓት ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች የሥነ-ልቦና ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል

63

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ተገቢው የሥነ-ልቦና ድጋፍ ሊሰጣቸው እንደሚገባ የመስኩ ባለሙያዎች ተናገሩ።

አሸባሪው ህወሓት በወረራ ይዟቸው በቆየባቸው የአማራና አፋር ክልሎች ንፁሃንን በግፍ ጨፍጭፏል፣ የግለሰብ ንብረቶችን አውድሟል።

ቡድኑ የህክምና ተቋማት ንብረትን ጭምር በማውደም ፀረ-ሕዝብ መሆኑን በግልጽ አስመስክሯል።

በተጨማሪውም የአሸባሪ ቡድኑ ታጣቂዎች ህጻናትን ጭምር አስገድዶ የደፈረ ሲሆን፤ የድርጊቱ ሰለባ የሆኑ ወገኖች ደግሞ ለከፋ ሥነ-ልቦናዊ ችግር መዳረጋቸውን ከተጎጂዎች የተገኘው መረጃ አመላካች ነው።

እነዚህም ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ካሉበት የሥነ-ልቦና ሆነ ማኅበራዊ ቀውስ እንዲወጡ የሥነ-ልቦና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ነው የመስኩ ባለሙያዎች ለኢዜአ የተናገሩት።   

በአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሥነ-ልቦና ሐኪም ዶክተር እንዳለ ማሞ፤ የመደፈር ጥቃት የደረሰበት ማንኛውም ሰው ለከፋ ጭንቀት እንደሚጋለጥ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ድብርት ውስጥ እንደሚገቡና ፍርሃት እንደሚሰማቸው ጠቁመው አንዳንዴም ራስን እስከ መጥላት የሚደርስ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገቡ ጠቁመዋል።

ስለዚህም ለእነዚህ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ከሚደረግላቸው መሠረታዊ ድጋፍ ጎን ለጎን የሥነ-ልቦና ድጋፍ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ተጎጂዎች የሥነ-ልቦና ድጋፍ ሳያገኙ ከኅብረተሰቡ ጋር በምንም መልኩ መቀላቀል እንደሌለባቸውም ጠቁመዋል።

በሆስፒታሉ ሌላኛዋ  የሥነ-ልቦና ባለሙያ ወይዘሮ ቀለሟ ሃይሌ በበኩላቸው በህጻናትና ሴቶች ላይ የደረሰው  ጉዳት እጅግ ከባድ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች ተጎጅዎችን በመርዳት ወደ ተስተካከለ ሥነ-ልቦናዊ ጤንነት እንዲመለሱ የመሥራት ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ሴቶቹ ከሚደርስባቸው ማኅበራዊ ቀውስ እንዲላቀቁም በዙሪያቸው ያሉ ቤተሰቦችና ሌሎችም የማኅበረሰብ ክፍሎች ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም