በጎ ፈቃደኛ ሃኪሞች በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን ለመርዳት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሊያቀኑ ነው

66

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጎ ፈቀደኛ ሃኪሞች በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን ለመርዳት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሊያቀኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር አስታወቀ።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በወራራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች በሚገኙ በርካታ የህክምና ተቋማት ላይ ዘረፋና ውድመት አድርሷል፡፡

በዚህም ነፍሰጡር እናቶችን፣ ህጻናትንና የህክምና ክትትል የሚሹ ዜጎችን ለከፋ ችግር ያጋለጣቸው ሲሆን፤ በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን መደገፍ ደግሞ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ለኢዜአ እንዳስታወቀው፤ በጎ ፈቃደኛ የህክምና ባለሙያዎች ጉዳቱ በደረሰባቸው አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው ህሙማንን ለማገልገል ዝግጁ ናቸው፡፡

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛው ማህበሩ በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ወረራ አካላዊና አእምሯዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመርዳት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአጭር ጊዜ በተደረገ ጥሪ ከ200 በላይ በጎ ፈቃደኛ ዶክተሮች ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለማገዝ መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

የማህበሩ አባላት በበጎ ፈቃደኝነት ወገኖቻቸውን ለማገዝ ቁርጠኛ መሆናቸውንም ነው ያነሱት፡፡

ማህበሩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የአስቸኳይ፣ የአጭርና የረዥም እቅድ አዘጋጅቶ የተጎዱ አካባቢዎችን ለመርዳት ወደ ስራ መግባቱንም ተናግረዋል።

ማህበሩ በተለያዩ አካባቢዎች ባለሙያዎችን መድቦ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ከሰኞ ጀምሮ ሃኪሞችን በመመደብ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በዘላቂነት ለማገዝም ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በአሸባሪው ህወሓት ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች ላይ የደረሱ ጉዳቶችን በመመልከት ተጨማሪ የቁሳቁስ ድጋፍ የማድረግ ስራው እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

አባላቱ ጉዳት የደረሳባቸውን ዜጎች ከመርዳት ባለፈ በውጭ ከሚኖሩ የህክምና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር የህክምና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የህክምና ባለሙያዎች በበጎ ፈቃደኝነት ግንባር ድረስ በማቅናት ዜጎችን ሲያገለግሉ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ከሶሰት ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

-አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም