ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት የስራ ኃላፊዎች ላይ ፍርድና ብይን ተሰጠ

85

ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ ያሬድ ዘሪሁን እና ሌሎች 24 ተከሳሾች ላይ ፍርድ እና ብይን ተሰጠ።

ተከሳሾቹ ከ1984 እስከ 2010 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ውስጥ በቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት በተለያዩ የስራ ሃላፊነቶች ተመድበው ሲሰሩ በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ማለትም በአዲስ አበባ ባሉ ክፍለ ከተሞች፣ በአማራ ክልል ባህርዳርና ጎንደር፣ በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ፣ ጅማ፣ ሻሸመኔና ቢሾፍቱ፣ በደቡብ ክልል ሀዋሳ ከተማ ሰዎች የሚታሰሩበትን ሁኔታ ማመቻቸታቸውና ድብቅ እስር ቤቶችና መመርመሪያ ክፍሎች እንዲዘጋጁ ማድረጋቸው ተጠቅሷል።በዚህም በማንኛውም ወንጀል የተጠረጠረን ሰው የመያዝ የማሰርና የመመርመር ስልጣን ሳይኖራቸው ከሽብር ወንጀል ጋር በተያያዘ ተጠርጥራችኋል በማለት በሌሊትና በቀን፣ ለወራትና ለዓመታት ከታሰሩበት ድብቅ እስር ቤቶች ውስጥ በላያቸው ላይ ውሃ እየደፉ፣ በአፍ ውስጥ ካልሲ በመክተት፣ የእግር ጥፍር በመንቀል፣ የተበዳዮችን የሰውነት ክፍል በኤሌክትሪክ በማስነዘር፣ እጅና እግርን በብረት ሰንሰለት በማሰርና ጠረጴዛ ላይ በመስቀል ሚስማር ባለው ጣውላ እንዲደበደቡ እንዲሁም በኤሌክትሪክና በሽቦ ገመድ እንዲገረፉ በማድረግ፣ ራቁታቸውን ጉንዳን ውስጥ በማስገባት፣ በብልታቸው ላይ ሃይላንድ በማንጠልጠል፣ በአፍንጫቸው እስክርቢቶ በመስደድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ስልጣንን አላግባብ በመገልገል የሚፈፀም ከባድ የሙስና ወንጀል መከሰሳቸው የሚታወስ ነው።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ እንደየተከሰሱበት አንቀፅ ጥፋተኝነታቸው በዐቃቤ ህግ ማስረጃዎች የተረጋገጠ በመሆኑ የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አቶ አፅበሃ ግደይ፣ አቶ አሰፋ በላይና አቶ ሽሻይ ልኡል አራት ተከሳሾች በሌሉበት የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁንና ሌሎች ተከሳሾች ከጠበቆቻቸው ጋር ቀርበው ብይኑን የተከታተሉ ሲሆን ተከሳሾቹ አንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።

ተከሳሾቹ በዋስ ወጥተን ክሳችንን እንከታተል ብለው ፍርድ ቤቱን ቢጠይቁም ዐቃቤ ህግ በዋስትና ጥያቄው ላይ በፅሁፍ አስተያየት ልስጥበት በማለቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ለታህሳስ 6 ቀን 2014 ዓ.ም መሰጠቱን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም