ዳያስፖራው በቀረበው ጥሪ መሰረት በከፍተኛ ቁጥር ወደ ሀገሩ እንዲገባ እና በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ጫና ለመቋቋም የሚያደርገው እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠል አለበት

135

ታህሳስ 2፣ 2014 (ኢዜአ) ዳያስፖራው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት በከፍተኛ ቁጥር ወደ ሀገሩ እንዲገባ እና በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ጫና ለመቋቋም የሚያደርገው እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ጥሪ አቀረቡ።

ባለፉት ሶስት ዓመታትም ከዳያስፖራው ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሃገር ቤት የተላከ መሆኑንም ገልጸዋል።

አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ዳያስፖራው እያከናወነ ያለው የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የሀብት የማሰባሰብ ንቅናቄን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ ውይይት ከሚመለከታቸው ዲፕሎማቶችና የዳያስፖራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ተወካዮች ጋር በበይነ መረብ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱም ከዚህ በፊት በነበረው ጊዜ በርካታ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡና በሀገራቸው ጉዳዮች ተሳታፊ እንዳይሆኑ ገደብ ተጥሎባቸው እንደነበር አስታውሰው፤ በሀገራችን ከመጣው ለውጥ በኃላ ግን ለዳያስፖራ ማህበረሰብ አዲስ አይነት የተሳትፎ በሮችንና የሀገር ባለቤትነት ዕድልን እንደፈጠረለት  አምባሳደር ብርቱካን ገልጸዋል።

በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታትም ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሃገር ቤት የተላከ ሲሆን ይህም በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠሩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ መሰማራቱንገልጸዋል።

ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተግባራት አንጻርም በውጤት የታጀቡ በርካታ እንቅስቃሴዎች ማከናወኑን ገልጸዋል። መንግስትም ዳያስፖራው ሊያበረክት የሚችለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲን በማቋቋም ተቋማዊ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ኢትዮጵያ ህዝቦቿ ለነጻነታቸው ባላቸው ቀናይነት አባቶቻችን በከፈሉት መስዕዋትነት ነጻነቷን አስጠብቃ መቆየቷን አውስተው፣ በአሁኑ ወቅትም የውስጥና የውጭ ኃይሎች በመተባበር በልዑላዊነቷ ላይ የደቀኑትን አደጋ ለመቀልበስ የአሁኑ ትውልድም መስዋዕትነትን በመክፈል የራሱን ደማቅ የታሪክ አሻራ በማስቀመጥ ቀጣይ ትውልዶች የሚያስታውሱት ተግባርን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

አክለውም ዳያስፖራው አንዳንድ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና በመቃወም፣ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ትግሉም እነዚህ ሀይሎችና ሚዲያዎቻቸው የሚያናፍሱትን የሀሰት መረጃ በማጋለጥ ባደረገው የተጠናከረ እንቅስቃሴ ትግሉ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካውያን ብሎም የሁሉም ነጻነት ናፋቂ ህዝቦች አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ የተዘጋጀውን መተግበሪያ በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለተደረገው ከፍተኛ ድጋፍም ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶ/ር አብይ አህመድ ዘመቻውን ለመምራት ወደ ግንባር መዝመታቸውን ተከትሎም ዳያስፖራው በቡድንና በተናጠል የግል ኑሮውን በመተው በአካል የትግሉን ጎራ በመቀላቀል ለሀገሩ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ ወደ ሀገር ቤት እንዲገባ የቀረበውን ጥሪ ተቀብሎ በከፍተኛ ቁጥር እንዲመጣ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።

 አያይዘውም ይህንን የሚያስተባብር በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ ብሄራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ በይፋ ስራ መጀመሩንም በወቅቱ አብስረዋል።

በሀገራችን ላይ የሚደረገው ጫና ቀጣይ ሊሆን እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ ዳያስፖራው እያከናወነ ያለውን የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የሀብት የማሰባሰብ ህዝባዊ ንቅናቄዎች አጠናክሮ እንዲያስቀጥል አምባሳደር ብርቱካን ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም