የኢትዮ-ቬትናም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ወደ ምጣኔ ሃብታዊ ትብብር ማሳደግ ይገባል ተባለ

62
አዲስ አበባ ነሀሴ 18/2010 የኢትዮጵያና የቬትናም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ወደ ምጣኔ ሃብታዊ ትብብር ማሳደግ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ። አፈ-ጉባዔዋ ይህን ያሉት ዛሬ ከቬትናም ፕሬዝዳንት ትራን ዳይ ኳንግን ጋር በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ትብብር መጠናከር በሚችልበት ሁኔታ ላይ በተወያዩበት ወቅት ነው። ወይዘሮ ሙፈሪያት እንደገለጹት የአገራቱን ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት መሰረት በማድረግ በመካከላቸው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከርና ምጣኔ ኃብታዊ ትብብርን ማሳደግ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያና ቬትናም በምጣኔ ኃብት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በግብርና በመሳሰሉት የልማት መስኮች በትብበር ለመስራት ከዚህ በፊት የፈረሟቸውን ስምምነቶች ሥራ ላይ ለማዋል የኢትዮጵያ ፓርላማ ትኩረት በመስጠት የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ አፈ-ጉባኤዋ ገልፀዋል። ቬትናም በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት፣ በልማት እና እድገት መስኮች ያላትን መልካም ተሞክሮ ለኢትዮጵያ እንድታካፍልም አፈ-ጉባኤዋ ጠይቀዋል። የሁለቱ አገራት ፓርላማና የፓርላማ አባላት ግንኙነትን ለማጠናከር መስራትም ተገቢ ነው ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት ይህም በአገራቱ መካከል ያለው ትብብር እንዲጎለብት እንደ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል። የቬትናም ፕሬዝዳንት ትራን ዳይ ኳንግን በበኩላቸው በኢትዮጵያና ቬትናም መካከል ጠንካራ የምጣኔ ሃብት፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብር ግንኙነት ለመፍጠር አገራቸው የበኩሏን ለመስራት ዝግጁ ናት ብለዋል። በአሁኑ ወቅት 11 ሚሊዮን ዶላር የሆነውን የአገራቱን የምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ለማሳደግ ቬትናም ፍላጎት እንዳላት ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት። በአገራቱ መካከል በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመስራት ከዚህ ቀደም የተፈረሙ ስምምነቶች ወደተግባር እንዲቀየሩ ቬትናም ትሰራለች ብለዋል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኩል ለዓለም ሰላም ባደረገችው አስተዋፆኦ ቬትናም ተጠቃሚ መሆኗን ገልጸው አሁንም በሰላም ማስከበር በመሳተፍ እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ አድንቀዋል። ቬትናም በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይም ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ መስራት እንደምትፈልግም ፕሬዝዳንት ትራን ዳይ ኳንግን ጠቁመዋል። የአገራቱ ፓርላማዎችም በመረጃና ልምድ ልውውጥ እንዲሁም በህግ አወጣጥ ላይ ተባብረው እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ቬትናም በቅርቡ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ትከፍታለች ያሉት ፕሬዚዳንቱ አፈ-ጉባዔ ሙፈሪያት ካሚል ቬትናምን እንዲጎበኙ ግብዣም አቅርበዋል። ለይፋዊ የስራ ጉብኘት ትናንት አዲስ አበባ የገቡት የቬትናም ፕሬዝዳንት ትራን ዳይ ኳንግን ከፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ውይይት ማካሄዳቻው ይታወቃል። በእስካሁኑ ቆይታቸው የኢትዮጵያና የቬትናም ግንኙነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ስምምነቶች ተፈርመዋል። ኢትዮጵያና ቬትናም በይፋ የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር መጋቢት 1976 ነው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም