የፍትህ ተቋማት ለሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች መከበር በልዩ ትኩረት መስራት አለባቸው

262

ታህሳስ 1/2014 /ኢዜአ/ የፍትህ ተቋማት ለሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች መከበር በልዩ ትኩረት መስራት እንዳለባቸው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አሳሰበ።

የፌደራል የፍትህ ተቋማት ጥምረት አለም አቀፉን የሰብአዊ መብት ቀን “የፍትህ ተቋማት ለእኩልነት እንቁም መድልዎን እናስወግድ የሰብአዊ መብቶችን እናስቀድም” በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው እለት አክብሯል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሰለሞን አረዳ፤ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የፍትህ ተቋማት በህገ መንግስቱና በአለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ የተመለከቱ ህጎችን የማከበር እና የማስከበር ከፍተኛ ሃላፊነት አለባቸው።

በመሆኑም የፍትህ ተቋማት ለሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች መከበር በልዩ ትኩረት መስራት እንዳለባቸው ምክትል ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ብርሀነመስቀል ዋጋሪ፤ ኢትዮጵያ በርካታ አለም አቀፍ ድንጋጌዎች እና ስምምነቶችን መቀበሏን ጠቅሰው የፍትህ ተቋማት በተለይም ለሰብአዊ መብት መከበር ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያ የሆኑት ምትኩ አለማየሁ በበኩላቸው ለሰብአዊ መብት መከበር የፍትህ ተቋማት ድርብ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

የፌደራል የፍትህ ተቋማት ጥምረት አለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ቀን የሃይማኖት አባቶች፣ የፖሊስና ሌሎች የፍትህ አካላት በተገኙበት ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ አክብሯል።