ተጎጂዎችን ከመርዳት ባለፈ የአሸባሪውን ቡድን የጥፋት ተልዕኮ ለማክሸፍ ድጋፋችንን እናጠናክራለን

68

ባህር ዳር፤ ታህሳስ 1/2014(ኢዜአ) የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት ተጎጂዎችን ከመርዳት ባለፈ አሸባሪው የህወሃት ቡድን የጥፋት ተልዕኮን ለማክሸፍ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡመድ ኡጅሉ አስታወቁ።

የጋምቤላ ክልል በአሸባሪው ወረራ  ለተፈናቀሉ ወገኖች 3 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብና እና አልባሳት ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን በርዕሰ መስተዳደሩ የተመራ ሉኡክ ባህር ዳር ከተማ በመገኘት ባስረከበበት ወቅት  አቶ ኡመድ ኡጅሉ እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሃት ለተወሰኑ ክልሎች ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያውያን ጠላት ነው።

ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት ሃገር ሲመራ በነበረበት ወቅት ዛሬ በአማራና አፋር ክልሎች እያደረገ ያለውን የዘር ጭፍጨፋ በጋምቤላ ህዝቦች ላይም ሲፈጽም መቆየቱን አስታውሰዋል።

ዛሬ ላይ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በከፈተው ጦርነት በአጎራባች የሚገኙ አፋርና አማራ ህዝቦች ላይ ታሪክ ሊረሳው የማይችል ጉዳት ማድረሱን አመልክተዋል።

በተለይም ንፁሃንን በመግደል፣ በማፈናቀል፣ ሃብት በመዝረፍና በማውደም ክፉ ጠላት መሆኑን በተግባር ማሳየቱን ነው ርዕሰ መስተዳደሩ የገለጹት።

የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት ተጎጂዎችን ከመርዳት ባለፈ  አሸባሪውን ቡድን  የጥፋት  ተልዕኮ ለማክሸፍ  የጀመሩትን ድጋፍ  አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ጌታቸው ጀምበር በበኩላቸው፤  አሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በከፈተው ጦርነት በርካታ ዜጎችን ለመከራና ለስደት ከመዳረጉም ባለፈ መሰረተ ልማቶችን ማውደሙን አውስተዋል።

የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት በአሸባሪው ቡድን ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች በመደገፍ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከጎናችን መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል ብለዋል።

ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ የቡድኑን እኩይ አስተሳሰብና የጥፋት ተግባር ለማምከን ኢትዮጵያውያን የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ኡመድ ኡጁሉ የተመራው ሉኡክ  ድጋፉን ለአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አስረክቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም