የርጥባን ዲፕሎማሲ መሿለኪያ አማራጮች …

270

(አየለ ያረጋል)

መግቢያ

በዲፕሎማሲ ቋንቋ ዘላቂ ወዳጅና ጠላት የለም። የዲፕሎማሲ መርህ ብሔራዊ ጥቅም ነው፤ የሉዓላዊነት ክብር ነው። ዓለም ላይ ሙሉ በኩልሄ ተፈጥሯዊ ጸጋ ያለው ምድር የለምና ፀጋን ተጋርቶ፤ ምርትን ተገበያይቶ፣ የጎደለን ተሞላልቶ፣ ተጠቃቅሞ የማደግ፣ የህዝቦችን ኑሮ የማረጋገጥ ጉዳይ ነው። ጥቂቶች ባለሀብቶች በሚዘውሯት፣ ጥቂት ሃያላን አዛዥ ናዛዥ ብዙሃኑ ደግሞ ምንዝር በሆነባት ዓለም ላይ ግን ይህ የዲፕሎማሲ መርህ ይጣሳል። በተለይም ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ወዲህ የአገራት የሃይል ሚዛኑ ተዛብቷል። ለአብነትም አሜሪካ መራሹ የሃያላን ቡድን የመጠቃቀም ግንኙነትን አዛብቶ፤ የዲፕሎማሲን መርህ ጥሶ ጣልቃ ገብነትና ጫና መፍጠርን መለያው አደርጓል። ዲፕሎማሲ የአራጣ አበዳሪና ተበዳሪ ግንኙነት ሆኗል። አበዳሪው እየከበረ፤ ተበዳሪው እየቆረቆዘ የሚድህበት የተቃርኖ መንገድ። ተጋግዞ መለወጥ ሳይሆን አንዱ ስመ-አጋዥ፤ ሌላው በርጥባን ሸክም ተንፏቃቂ ሆኖ መቀጠል አለበት የሚል ያልተጻፈ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተሰምሯል። ይህም ርጥባን ተጠቅሞ አገሮችን  አንገቱ ላይ ገመድ እንደተጠለቀለት ውሻ በራስ ርምጃ የማንቀሳቀስ የቅኝ ገዥዎች ገመድ ነው። በእርዳታ ሰበብ እንዳሻው ማሾር፣ አልሾርም ካለም የማሰሪያ ገመዱን ተጠቅሞ ማሽመድመድ፣ የአገራትን መንግስታት ማፈራረስ፣ አፈንጋጭ የሚሏቸውን መሪዎች ማስወገድ ገሃዳዊ ስልት ነው። ይህ አይነቱ ስልት ገቢራዊ የሚደረግባቸው፤ ጫናው የሚበረታባቸው የተመረጡ አገራት ደግሞ አሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከዓለም ሃያላን ጥርስ ውስጥ የገባች በዲፕሎማሲው መስክ የምዕራቡ ዓለም እንዳሻው ሊጫወትባት የሚሻት አገር ነች። በርጥባን ከሚሞከር ዲፕሎማሲያዊ ጫና ባሻገር ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጠረው ጫና እና የጣልቃገብነት ግብግብ አንድምታ መልከ ብዙ ነው። በአንዳንድ ነጮች የተቄመባት ጥንታዊት አገር ናትና።

የአንዳንድ ምዕራባዊያን ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ አቋም እና ዳራው

በቀዳማዊ አጼ ኅይለስላሴ ዘመነ መንግስት አማካሪ የነበሩት አሜሪካዊ ጆን ስፔንሰር ስለኢትዮጵያ በጻፉት መጽሐፋቸው ‘ጥርስ የገባች አገር /Ethiopia at bay‘ ብለዋታል። በርግጥም ይህ ሐረግ ኢትዮጵያን በእጅጉ ይገልጣታል። ኢትዮጵያ ዛሬም ኅያላኑ መንጋጋቸው ውስጥ አስገብተው ለማኘክ የሚቋምጡላት የምንጊዜም ምኞታቸው ናት። ጥርሳቸው ውስጥ አልታኘክ ብላ ያስቸገረቻቸው ‘ጥሬ‘ ነች። ምድረ ቀደምቷ አፍሪቃዊት አገር ኢትዮጵያ በአንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ዐይን በጎ እይታ የላትም። የመንስኤውን ዳራ ተንታኞች ሲገልጹ በነጮች ቅኝ ግዛት ቀንበር ያለመንበርከክ ገድሏን በቀዳሚነት ይጠቅሳሉ። አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደጠቀሱት ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ በነኦቶማን ቢስማርክ አፍሪካን የመቀራመት የበርሊን ስምምነት በብቸኝነት በቅኝ ግዛት አለመያዟ ዛሬም ጥርስ ውስጥ እንደገባች ቀጥላለች። ይህም የአድዋ ድል ነው። የአድዋ ድል አራት ሰዓት በፈጀ ጦርነት የተገኘ ድል በሚል ብቻ የሚታለፍ አይደለም። አድዋ በሰው ልጆች አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ፣ የአስተሳስብ ፍልስፍና የለወጠ፣ የቅኝ ገዥዎችን ሞራል የሰበረ፣ ለጭቁን ጥቁር ህዝቦች ደግሞ የነጻነት ጮራ የፈነጠቀ ድል ነው።

በሌላ በኩል የፀረ ኢትዮጵያ አቋም መንስኤው በተፈጥሮ ያላት ጂኦ ፖለቲካዊ አቀማምጥ ነው። የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የዓለም 60 በመቶ ንግድ በሚንቀሳቀስበት የቀይ ባህር ወይም የባብኤል መንደብን በመያዝ የዓለምን ኢኮኖሚ ለመቆጣጠር የማይተካ ሚና አለው። ጅቡቲ ውስጥ በጦር ሰፈር ግንባታ የሚደረገው ግብግብም ከዚህ ምስጢር የመነጨ እነደሆነ እሙን ነው። የአፍሪቃ ቀንድ ሀብት መቀራመትም የምዕራቡ ዓለም ሌላው የባዕዳን ተልዕኮ ነው። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንቀሳቃሽ ሞተርነቷ ባለፈ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧና የህዝብ ብዛቷ በዚህ ቀጣና ላይ ቀስ በቀስ እያደገች ከመጣች ለምዕራባዊያን ስጋት ትሆናለች የሚል ፖሊሲ ቀርጸዋል። በሌላ በኩል የስዊዝ ካናል ከተከፈተ በኋላ ግብጽ ለምዕራባዊያን ጥቅም ወሳኝ አገር ሆናለች። በዚህም አንዳንድ ምእራባዊያን ኢትዮጵያ የራሷ የተፈጥሮ ሀብት በሆነው የአባይ ወንዝ እንዳትጠቀም ለዘመናት ስታሴር ለኖረችውና እያሴረች ላለችው ግብጽ ወግነዋል። ስለዚህ የአባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ጉዳይ አንድም የኢትዮጵያ ዕድገት ስለማይፈለግ፤ አንድም ግብጽን ላለማስከፋት ሲባል አንዳንድ ምዕራባዊያን ኢትዮጵያ ፈጣሪ ከቸራት የወንዝ ጸጋዋ ውሃ እንዳትጠጣ ሁሉን አቀፍ ዘመቻ ከፍተውባታል።

እናም በድሕረ አድዋ ድል በየዘመኑ ኢትዮጵያን ወግተዋል። ከአድዋ ድል 40 ዓመታት በኋላ የተነሳው የፋሺስት ኢጣሊያ መንግስት የግፍ ወረራ ሲፈጽም አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም መንግስታት ኢትዮጵያን የመስዋት በግ አድርገዋታል። አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ለራሳቸው ጥቅም (ሞሶሎኒ ወደ ሂትለር እንዳይወግን ለማባበል) ሲሉ ኢትዮጵያን ለፋሺስት አሳልፍው ሰጥተዋል። ታሪክ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያዊያን በዓለም በተከለከለ ጅምላ ጨራሽ አደገኛ መርዝ ሲጨፈጨፉ የአሜሪካና እንግሊዝ ኩባንያዎች ለሞሶሎኒ መንግስት የጦር መሳሪያ ሽያጭ ላይ ነበሩ። ጣሊያን ምንም እንኳ የራሷ ጦር መሳሪያ የማምረት አቅም ቢኖራትም በኢትዮጵያ ላይ የተጠቀመቻቸው  መሳሪያዎች ግን የራሷ ምርቶች ብቻ አልነበሩም። እናም በተዘዋዋሪ ማዕቀብ ተጣለ ቢባልም ኢጣሊያ ግን የፈለገችው ይቀርብላትና ታመርትም ስለነበር ማዕቀቡ ለእሷ ምንም ነበር። በተቃራኒው ዘመናዊ መሳሪያ ያልነበራት ኢትዮጵያ በምዕራብ አገራት በሚዘወረው የዓለም መንግስታት ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) ማዕቀብ ተጥሎባት የከፈለችበትን መሳሪያ ሳይቀር ወደ አገር ቤት እንዳታስገባ ተከልክላለች። ከነጻነት ማግስት የግዛት አንድነቷ እንዳይጠበቅ ከጀርባ ወግተዋታል። ግዛቷን እንዲቆራረስ ጥረዋል፤ ግረዋል። ኢትዮጵያ የባዕዳን ዕኩይ ተልዕኮ ቤተ ሙከራ ነች-ምንም እንኳ በየዘመኑ በልጆቿና በወዳጆቿ መርዛቸው እየረከሰ እና እየከሸፈ ቢዘልቅም!!

እናም ኢትዮጵያ የሕልውና አደጋ ሲደቀንባት ዘመናትን የተሻገረ ነው። የዘንድሮ የሕልውና አደጋ አዲስ አይደለም። አንዳንድ ምዕራባዊያን መንግስታት ኢትዮጵያን ለማፈራረስና ለማዳከም ያልሄዱበት ርቀት፣ ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልቆፈሩት ጉድጓድ አልነበረም። አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና አንዳንድ ምዕራባዊያን መንግስታት በኢትዮጵያ ላይ ሁለንተናዊ ጫና ጅማሮ ከትናንት የጀመረ ነው ባይ ናቸው። የደብረ ብርሐን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ውብአንተ አያሌው ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲና ዕድገት የምታደርገው ጉዞ ያልጣማቸው አንዳንድ ምዕራባዊያን መልከ ብዙ ጫናዎችን የጀመሩት ዛሬ አይደለም የሚለውን ሀሳብ ይደግፋሉ።

ከኢትዮጵያ ጋር በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ግንኙነት የጀመረችው አሜሪካ የተሻለ የዲፕሎማሲ ጅማሮ ቢኖራትም ቀስ በቀስ ግን ወዳጅ መስላ በሴራ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ስታብር ኖራለች፤ ዛሬም ቀጥላለች። በ5ቱ ዓመት የፋሺስት የግፍ ወረራ ኢትዮጵያን ክዳለች። በ1953 መፈንቅለ መንግስት በዲፕሎማቶቿ በኩል የሴራው ተሳታፊ እንደነበረች የጻፉ የታሪክ እማኞች አሉ። በ1969 ዓ.ም የዚያድባሬ ወረራም ሆነ ከዛ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ የተደቀነባትን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ የተሻለች ወዳጅ አገር የነበረችው አሜሪካ ለእርዳታ ብትጠየቅም ፊቷን አዙራለች። ይልቁንም ኢትዮጵያ የገዛችውን የጦር መሳሪያ እንዳታስገባ ነፍጋለች። በለሌ በኩል ተገንጣይ ቡድኖችን በመደገፍ የግዛት አንድነቷ እንዲናጋ በተቃራነው ቆማለች። አሜሪካ በየዘመኑ በዲፕሎማሲ ስም ሰላዮቾቿን ወደ ኢትዮጱያ ቤተ መንግስት በመላክ ኢትዮጵያን ስትቦረቡር ኖራለች። ከኢትዮጵያ ለትምህርት አሜሪካ የሄዱ ኢትዮጵያዊያንን በሲ.አይ.ኤ መረብ ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያን ለመበታተን በእጅጉ ሰርታለች። በተለይም በድርግ ዘመነ መንግስት ፀረ ኢትዮጵያ ኃይላትን በማደራጀት፣ ከፍተኛ ባለስልጣናትን በማስኮብለል የደርግ መንግስትን ለመጣል ከመስራት ባለፈ ኢትዮጵያን ከፋፍላ ለመበታተን ኳትናለች። የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር/ትሕነግ/ ወደ ስልጣን እንዲመጣ ሚናዋ ጉልህ ነበር። የኢትዮጵያ አራሙቻ የሆነውን የወያኔን ስርዓት ኮትኩታ አሳድጋለች። አሁንም በድርቀት ላይ ያለውን የኢትዮጵያ አረም የሆነው አሸባሪ ቡድን ዳግም በኢትዮጵያ ላይ እንዲበቅል እስከ ጥግ ድረስ እየኳተነች ነው። ሽብርተኞችን የምትደግፍ፤ በህጋዊ መንግስታት ላይ ደግሞ ማዕቀብ የጣለች አገር ነች-አሜሪካ።

አሜሪካ በመንግስታቱ ድርጅትና በአውሮፓ በኩል በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ እንዲጣል  በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጥረት ስታደርግ ስለመቆየቷ ምሁራኑ ይገልጻሉ። በዚህ ዓመት መጀመሪያም በአዲስ መንግስት ምስረታ ዋዜማ ተናጠላዊ ማዕቀብ መጣሏ አይዘነጋም። አሜሪካን ለአብነት አነሳን እንጂ እንግሊዝና መሰሎቿ የአውሮፓ አገራትም ከዚህ የተለየ ተልዕኮ የላቸውም።

ከርጥባን ዲፕሎማሲ መሿለኪያ አማራጮች

ይህቺ መከራ የጣፋት የምትመስል ኢትዮጵያ እንደ ጠላቶቿ ብዛትና ጭካኔ መውጫ መንገዱ ጠፍቷት አያውቅም። ዛሬ የኢትዮጵያን ሕልውና የተፈታተነው የምዕራብ ዓለም የኃያላን ቡድን የራሱን ጦር ከማስገባት በስተቀር ያልሞከረው የጣልቃ ገብነት ድርጊት የለም። ወዳጅ አገራት ግን ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ ውለታ እየዋሉላት ነው። አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ነጻ የገበያ ዕድል (አጎዋ) ብትሰርዝም ቻይና የአፍሪካ የግብርና ምርቶችን መገበያያ ነጻ ገበያ ማመቻቸቷን ይፋ አድርጋለች። አሜሪካ ዜጎቿን ውጡ እያለች ስትጣራ ቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ወደ ኢትዮጵያ ልካለች። ይህን ያህል ዜጎች በኢትዮጵያ ከሌሏት አሜሪካ ይልቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ሌት ተቀን በስራ ላይ የተጠመዱ ዜጎች በኢትዮጵያ ያሏት ቻይና የምዕራቡን ስሁት መንገድ በመረዳት ‘ኢትዮጵያ ሰላም ነች፤ በኢትዮጵያ ያላችሁ ቻይናውያን ስራችሁን ቀጥሉ’ ብላለች።

አጎዋ አሜሪካ በታዳጊ አገራት ላይ የፖለቲካ ፍላጎቷን ለማስፈፀም ቁልፍ መሳሪያዋ እንደሆነ ዶክተር ውብአንተ ይናገራሉ። በተቃራኒው የቻይና የወቅቱ የግብርና ምርቶች ነፃ ገበያ ዕድል ማመቻቸቷ ከዚህ የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈፀሚያ ለመላቀቅ የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል ይላሉ። የርጥባን ዲፕሎማሲ ግንኙነት የሚያመጣውን ጫና ለመቋቋም አማራጭ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እንደሚሆንም አምባሳደር ጥሩነህ ይስማማሉ። እናም የምዕራቡ ዓለም ጫና ሌሎች ያልታሰቡ ዕድሎችን እየፈጠረ ያለና የአፍሪካን እና የምስራቁን ዓለም የንግድ ግንኙነት በአዲስ ምዕራፍ የሚያጠናክር እንደሆነ ገልፀዋል። በርግጥም በርካታ የምዕራባዊያን ተንታኞች ሳይቀር የአሜሪካ የተሳሳተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለታዳጊ አገራት ከቻይና ጋር ያላቸውን የመጠቃቀም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጠናክር፣ የምዕራቡን የርጥባን ግንኙነት የሚቀንስ እንደሚሆን እየገለፁ ይገኛሉ።

የታሪክ ባለውለታዋ ሩስያም የአንዳንድ ምዕራባዊያንን ጣልቃ ገብነትና ጫና በይፋ ኮንናለች። ሩስያ በአፍሪቃ ቅኝ ግዛት እሳቤ አልነበራትም። በርጥባን ፖለቲካ ጥቁሮችን አልበዘበዘችም። እንደአሜሪካ በተሳሳተ ፖሊሲ ሌሎች አገራትን አላፈረሰችም። በየዘመናቱ አንዳንድ ምዕራባዊያን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በቀጥታም ሆነ በተጋላቢዎቻቸው በኩል ወረራ ሲፈፅሙ ሩስያ ከጎናችን ነበረች ይላሉ አምባሳደር ጥሩነህ። በርግጥም አፍጥጦ የመጣው ቅኝ ግዛት አደዋ ላይ ድል ተነስቶ ሲመለስ ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጎን የሩስያ ቀይ መስቀል ነበር። በ5ቱ ዓመት የግፍ ወረራ ወቅትም ሩስያ ከምዕራባውያን በተቃራኒ ከኢትዮጵያ ነጻነት ጎን የቆመች ባለውለታ ወዳጅ አገር ነች። ሩስያ በአጭሩ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ሚዛን ስታስጠብቅ ኖራለች፤ ዛሬም ቀጥላለች። በዚያድባሬ ወረራ ሩስያ፣ ኩባና የመንን የመሰሉ ወዳጅ አገራት ባይኖሩ ኖሮ ኢትዮጵያ ከአቅሟ በላይ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀችውን የታላቋ ሶማሊያ ወረራ በቀላሉ መቀልበስ ባልቻለች ነበር።  

የእነዚህ ወዳጅ አገሮች የችግር ጊዜ አጋርነት በርግጥም ለኢትዮጵያ ከርጥባን ዲፕሎማሲ መሿለኪያ አማራጭ መስመር እያሰመሩ ይመስላል። በአምባሳደር ጥሩነህ እና በዶክተር ውብአንተ እምነት በመንግስታቱ ድርጅት ፀጥታው ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው ቻይናና እና ሩስያ እየተጫወቱ ያለው ሚና ለኢትዮጵያ ሕልውና መረጋገጥ፤ ለምዕራባውያን ሴራ መክሸፍ ከፍተኛ ነው። ምዕራባውያን በታሪክ አጋጣሚ በተቆጣጠሩት ዓለምን የመዘወሪያ ተቋማቸው ውስጥ በየወቅቱ በኢትዮጵያ ላይ ይዘውት የሚቀርቡት የውሳኔ ሀሳብ ሁሌም ሉዓላዊነትን የጣሰ፤ ዓለም አቀፍ ሕግን የተጻረረ ነው። አሜሪካ በየጊዜው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የምታደራጃቸው የባንዳዎች አደረጃጀትም (በቅርቡ በአሜሪካ የተስተዋለው የሽግግር መንግስት ተብዬው መስራች ቡድን እና የሕወሃት ወዳጆች ጡረተኛ ዲፕሎማቶች ድብቅ ስብሰባን ልብ ይሏል) ሌላው የምንጊዜም ፀረ ኢትዮጵያ አቋማቸው ማረጋገጫ ነው።

ዓለም ከግማሽ ምዕተ ዓመታተ በፊት በሁለት ሃይላት ጎራ ስትመራ ብትቆይም ዛሬ ላይ ግን በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ የዳበሩ አያሌ ሃይላት እንደተፈጠሩ አምባሳደር ጥሩነህ ይገልጻሉ። ኢትዮጵያን ከድህነት ማውጣት ላይ በማተኮር በዲፕሎማሲያችን የትኛው አገር የተሻለ ጥቅም ይሰጠኛል የሚለው መታየት ይኖርበታልም ይላሉ። እናም ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲዋ መቃኘት ያለበት ከምዕራብም ሆነ ከምስራቅ ከጥቅሟ አንፃር ብቻ መሆን አለበት ይላሉ። ስለዚህ በዚህ ወሳኝ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን የወገኑ ቻይና፣ ሩስያ እና መሰል አገራት ጋር ዲፕሎማሲን ማጠናከር ያሻል። ይህም የአንዳንድ ምዕራባዊያንን ሁሉን አቀፍ ጫና ለመቋቋም ያስችላል ባይ ናቸው ባለሙያዎቹ። ከሁለቱ አገራት በተጨማሪ ኃይል የገነቡ በርካታ አገራት ስላሉ ከእነዚህ ኃይሎች ጋር ወዳጅነትን በማጠናከር ሊደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ መቋቋም ይገባል ብለዋል።

የጥቁሮች አጋርነት-ብዙ ያልተራመደችበት የዲፕሎማሲ ፍኖት

ቀለም ተኮር ልዩነትና ጭቆና የትናንት ቅኝ ገዥዎች ታሪክ ብቻ አይደለም። የሰዎች የቀለም ተኮር መድሎ ዛሬም በጥቁሮች ላይ በጉልህ ይንጸባረቃል። በተዘዋወሪም ሆነ በቀጥታ የነጮች ሁሉን አቀፍ ጫና አለባቸው። ይህ የጥቁሮች ጥላቻ ከግለሰብ እስከ አገር፤ ከአገር እስከ አህጉር የተለጠጠ ቴክኖሎጂ ያልፈወሰው የትናንት ደዌ ነው። ይህ ያስቆጣቸው የመላው ዓለም ጥቁሮች ትልቅ ተጋድሎ አድርገዋል፤ በዘመናት ተጋድሎም ለውጥ አምጥተዋል። ያም ሆኖ ዛሬም በጥቁሮች ላይ መዋቅራዊ ጭቆና አልተገታም። የዕጅ አዙር ቅኝ ግዛት በርትቶ ቀጥሏል። ምዕራባዊያን ትናንት የጨለማው አህጉር ሲሉት የነበረው አህጉረ-አፍሪካን ጨለማ ሳይሆን የብርሐናቸው ፊውዝ መሆኑን አላጡትም። የጥቁሮች ትብብርና መሰባሰብ ለአንዳንድ ምዕራባዊያን አደጋ ነው። እናም ጎረቤት አገራትን ማናከስ፣ የጥቁሮችን አንድነት መስበር፣ ዘመን ተሻጋሪ የጥላቻ አጥር መገንባትን ትኩረት ያደርጋሉ። ለዚህ የቅኝ ግዛት እሳቤ የማይጥማት ኢትዮጵያም ለዚህ ፖሊሲያቸው ፀር ተደርጋ ትቆጠራለች። ለጥቁሮች ንቅናቄ፣ መሰባሰብና ነጸነት ፋና ወጊ ናትና።

ኢትዮጵያ ለመላው ጥቁር ህዝቦች የነጸነት እና የትግል ፋና ወጊ መሆኗን አምባሳደር ጥሩነህ ይጠቅሳሉ። ድሕረ አድዋ ድል ኢትዮጵያዊነት በባርነት ውስጥ ለነበሩ የዓለም ጥቁሮች ሁሉ ማታገያ ትዕምርት ነበር። ዛሬም በአፍሪካ እና በአሜሪካ በኢትዮጵያ ስም የተቋቋሙ ተቋማት ሕያው ማሳያ ነች። በርካታ አፍሪካ አገራት የሰንደቅ ዓላማዋን ቀለማት ወርሰዋል። የመሰባሰቢያ አዳራሻቸውን/የአፍሪካ ሕብረት/ በነጻነት ትዕምርታቸው ደጃፍ አዲስ አበባ እንዲሆን ፈቅደዋል።

በፀረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄ ኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ ነበራት። ለነጻነት ታጋዮች ምስካይ/መሰባሰቢያ እንደሆነችም ኔልሰን ማንዴላ እና ጆሞ ኬንያታን ማውሳት በቂ ነው። ለዚህም በጥቁሮች ዘንድ ኢትዮጵያ በ1928ቱ የፋሺስት የግፍ ወረራ ሲፈጸምባት በምዕራባዊያን አገራት የነበሩ የመላው ጥቁሮች ልሂቃን ከጎኗ ተሰልፈው ተሟግተውላታል። ጋዜጠኛ ጀፍ ፔርስ ‘የአርበኞች ጀብዱ’ በተሰኘው በአምስት ዓመት ወረራ ላይ በሚያተኩረው የታሪክ መጽሐፉ ላይ እንዳሰፈረው የግፍ ወረራ በተፈጸመባት ወቅት ጥቁሮች ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈው በአውሮፓና በአሜሪካ ወረራውን አውግዘዋል። የገንዘብ ማሰባሰብ ስራዎችን አከናውነዋል። በተለያዩ አገራት ቪዛ ቢከለከሉም ወደ ኢትዮጵየ ገብተው ለመዋጋት ቆርጠው ተነስተው ነበር። (ኮሎኔል ጆን ሮቢንሰን መሰል ጥቁር አሜሪካዊ ባለውለታዎች ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈው ጠላትን ተዋግተዋል) በኢትዮጵያዊ ዶክተር መላኩ በያን መሪነትም በአገረ አሜሪካ አፍሮ-አሜሪካኖች በኢትዮጵያ ስም ሰፊ ንቅናቄ አካሂደዋል፤ ድጋፍ አሰባስበዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት በተለየ በትልቅ አርዓያነትና ተምሳሌትነት ትወሰዳለች። ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች፣ ቀደምት ስልጣኔን ካልተበረዘ ማንነት ጋር የያዘች፣ የራሷ ቀለምና ፊደል ያላት፣ የሺህ ዓመታት ታሪክ ያላት አገር ብትሆንም ይህን ዕድል ግን በጥቁሮች ዲፕሎማሲ በሚገባ አልተጠቀመችበትም ብለዋል ባለሙይዎቹ። ዛሬ መሰል ችግር ሲገጥማት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የጋራ ስልጣኔና ማንነት የጠበቀች አገር መሆኗን በማስገንዘብ ከአፍሪካዊያን ጋር አብሮ መሰለፍ የወቅቱ አንኳር የዲፕሎማሲ አማራጭ መሆኑን አምባሳደር ጥሩነህ ገልጸዋል። አፍሪካ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን በላይ ህዝብ ያላት እንደመሆኗ አፍሪካዊያንን በማነቃነቅ ከርጥባን ዲፕሎማሲ እንዲላቀቁ ማስተባበር፣ ከዘመናዊ ቅኝ ግዛት (ኒዮ-ኮሎኒያሊዝም) እንዲወጡ የቀደምት መሪነቷን ሚና መጫወት ይገባታል። የጥቁሮች የትብብር ዲፕሎማሲ ከርጥባን ዲፕሎማሲ መውጫ መንገዶች አንዱ አማራጭ ይሆናል። በተለይም በዚህ ወቅት በመላው ዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ ጥቁሮችን ከኢትዮጵያ ጎን ማሰለፍ ትርፉ ብዙ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን በላይ ህዝብ ያላት አፍሪካ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ (ድምጽ በድምጽ የመሻር መብት ካለቸው ተርታ) ሊኖራት እንደሚገባ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በይፋ ጠይቀዋል። የአፍሪካዊያን የጋራ ቤት የሆነችው ኢትዮጵያ እንዲህ መሰል የአፍሪካዊያን ንቅናቄ ማስተባበር በርግጥም ወሳኝ እርምጃ ሳይሆን አልቀረም። ሌሎች አፍሪቃዊ አገራትም ይህን የምዕራብ መራሽ አድራጊ ፈጣሪነት 'በቃ' ካሉ የአፍሪካ ራስን በራስ የማስተዳደር፣ ከርጥባን የምዕራብ ዓለም ፖለቲካ ፍኖቷ የመውጫ ተስፋዋ ይለመልማል።

ልክ ከ80 ዓመታት በፊት እንደነበረው ሁሉ ዛሬም አንዳንድ ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ለይ እያደረጉት ያለውን ሁሉን አቀፍ ዘመቻ የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ ነው። በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ በሚሊኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የ’በቃ’(no more) ንቅናቄን አቀጣጥለውታል። ይህም የጥቁሮችን ቀልብ ስቧል። አፍሪቃ ልሂቃንንም ከአውሮፓ አገራት የእጅ አዙር ተዕጽኖ እንላቀቅ በሚል የ‘በቃ’ የማህበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ ማቀንቀን ጀምረዋል። ይህን ንቅናቄ የማስፋፋትና አገራትን ከኢትዮጵያ ጎን ለመሰለፍ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ትልቅ የቤት ስራ ነው።

በተለይም የ'በቃ'/no more/ ንቅናቄ አንድምታው እና አወንታዊ ሚናው ጎልብቷል። ምንም እንኳ የአሜሪካው የቲውተር ካምፓኒ ዕገዳ ቢጥልም ተፅኖናው ግን በሰልፍም ሆነ በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞች መነቃነቅን በመፍጠር የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገው ጫና እንዲገታ እያደረገ ነው። ሌሎች አገራትን እንዳፈራረሰው ሁሉ በኢትዮጵያ ላይ ለመድገም የውሃ ቀጠነ ሰበብ በመፈብረክ ዘርፈ ብዙ ጫናዎችን እያደረገ ቢሆንም እየተሳካለት ግን አይደለም። ለአብነትም መሬት ላይ የሌለ ሀሰተኛ መረጃ በመፍጠር የትግራይ ዘር ማጥፋት የተሰኘ ልቦለድ የተጻፈ አዋጅ በዚህ ንቅናቄ መሰረት በአገሪቱ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እንዳይፀድቅ ተደርጓል። በድምጽ በካርድ የመቅጣት ንቅናቄ፣ ኢትዮ- አሜሪካኖች እንደ ዜግነት መብታቸው በአሜሪካ ፖለቲካ የሚያደርጉት ንቁ ተሳትፎም ዘመን ተሻጋሪውን ጸረ-ኢትዮጵያ አቋም ማለሳለሱ አይቀርም።

ሲጠቃለል ..

የኢትዮጵያ ህዝብ በየዘመናቱ የተፈተነ መጥፎ ጊዜያትን እንድ ሆኖ የተሻገረ፣ ፋሽዝምን ያለፈ ጠንካራ ህዝብ ነውና አሁናዊ ችግሩንም እንደሚጣው እርግጥ ነው። አንዳንድ ምእራባውያን በኢትዮጵያ ላይ ጥቁር ከል ቢደርቡባትም አፍሪቃዊያንና ሌሎች ወዳጆቿ የክብርና የተስፋ ካባ መደረባቸው አይቀርም። የኢትዮጵያ ጠላቶች እንደአሸን ቢፈሉም ባንዳዎች ቢበረክቱም በቁርጥ ቀን ልጆች ግን ብልጽግናዋ እውን ይሆናል። ታሪክ እንደሚነግረንም ሁል ጊዜ አንድ እውነት አለ፤ የኢትዮጵያ አሸናፊነት።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም