ብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ለመገንባት ከውጭ ድርጅቶች ጋር ሥምምነት ተፈረመ

64

ታህሳሥ 1/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፈረንሳዩ ጀኔራል ኤሌክትሪክ እና ከቻይናው ሲኖ ሃይድሮ ኩባንያዎች ጋር ብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ለመገንባት የሚያስችለውን ሥምምነት ተፈራርሟል።

ሥምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ፣በምስራቅ አፍሪካ የጀኔራል ኤሌክትሪክ ንዑስ ቀጣና የሽያጭ ኃላፊ ማንያዘዋል ተስፋዬ እና የሲኖ-ሃይድሮ ተወካይ ሚስተር ቲያን ሆንግጁን ናቸው።

ሥምምነቱ ሁለት ብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከላት ግንባታዎች የማከናወን እንዲሁም በሁሉም የኃይል ማመንጫ እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የመቆጣጠሪያና ለክትትል የሚረዱ ሥርዓቶችን የመዘርጋት ሥራዎችን ያጠቃልላል።

የፕሮጀክቱን ግንባታ ጀኔራል ኤሌክትሪክ እና ሲኖ ሃይድሮ ኩባንያዎች በጋራ የሚያካሒዱት ሲሆን የማማከር ሥራውን ደግሞ ሒፋብ የተባለ የፊንላንድ ኩባንያ እንደሚያከናውን በሥምምነቱ ላይ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሥራ የሚገባ ሲሆን ለዚህም ከ57.67 ሚሊዮን ዩሮ እና ከ102 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞለታል።

የፕሮጀክቱ የፋይናንስ ወጪ 1/3ኛው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተቀረው 2/3ኛው ደግሞ በፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ እንደሚሸፈን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም