የኢትዮጵያን ህልውና በማስከበር ብልጽግናዋን እናረጋግጣለን

79

ድሬዳዋ ፤ ህዳር 30/2014 (ኢዜአ) በህብረ-ብሔራዊ አንድነት የኢትዮጵያን ህልውና በማስከበር ብልጽግናዋን እናረጋግጣለን ሲሉ የ16ተኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ተሣታፊዎች አስታወቁ።

ትላንት በድሬዳዋ የተከበረው 16ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን  ተሳታፊዎች "በአሸባሪው ህወሃት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳትና መልሶ ለማቋቋም ኢትዮጵያዊያን ከጫፍ ጫፍ እያደረጉ የሚገኙት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ሲሉም ለኢዜአ ተናግረዋል ፡፡

ከኦሮሚያ ክልል የበአሉ ተሳታፊ አቶ አሊ ሁሴን እንዳሉት የዘንድሮ በዓል ኢትዮጵያዊያን ህብረ-ብሔራዊ አንድነታቸውን አጽንተው አሸባሪዎቹን የህውሃትና ሸኔን ሀገር የማፍረስ ሴራ እያከሸፉ  ባሉበት ወቅት መከበሩ ኢትዮጵያዊ ህብረት እንዲደምቅ አግዟል፡፡

የአሸባሪዎቹን ሀገር የማፍረስ ሴራ ለማምከን የተጀመረውን የዘመቻ ህብረ ብሄራዊ አንድነት በማጠናከር የኢትዮጵያን ልማትና ብልጽግና  ለማረጋገጥ እንደሚተጉ ተናግረዋል፡፡

ከጋምቤላ ክልል ተሳታፊ የሆኑት  አቶ ከድር አኩማ በበኩላቸው "በአራቱም መአዘናት የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን በተባበረ ክንድ የአገር ጠላት የሆነው አሸባሪው ህውሃት የከፈተውን ጦርነት ለመመከት የጀመርነውን ትግል አጠናክረን ለመቀጠል በዓሉ ልዩ አጋጣሚ ፈጥሯል" ብለዋል፡፡

የጋምቤላ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላምና ፀረ-ህዝብ ታጣቂ ቡድኖችን ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ከመታገልና ሰላምን ከማስጠበቅ ባለፈ  የኢትዮጵያ ብልጽግና እንዲረጋገጥ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

 "ወጣቶች ከአገር መከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የጸጥታአካላት ጎን በመሰለፍ አገርን ከሽብርተኞች ከማዳን ባሻገር በክልሉ ያሉ ዘራፊዎችንና ህዝብን የሚያፈናቅሉ  ሽፍቶችን  ለህግ እያቀረብን የኢትዮጵያ ሠላምና ልማት እንዲረጋገጥ እየሰራን ነው"  ያለው ደግሞ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የበዓሉ ተሳታፊ ወጣት ናስር ደጉ ነው፡፡

ከበዓሉ አዘጋጅ ድሬዳዋ ከተማ  የተሣተፉት አቶ ፈቲህ መሐመድ በበኩላቸው "ህዝቡ አሸባሪው ህውሃት ያቀዘቀዘውን የድሬዳዋ ፍቅርና ህብረት በመመለስ አካባቢውንና አገሩን ወደ ብልጽግና ለማሻገር እያደረገ ያለው ርብርብ ተጠናክሮ ቀጥሏል " ብለዋል።

"በተለይ ወጣቱ ከበሬ ወለደ አሉባልታ ሊርቅ ይገባል" ያሉት አቶ ፈቲህ "ሁላችንም ከተባበርን እኛን ኢትዮጵያውያንን የሚያሸንፍ ሃይል የለም" ሲሉ በጽእናት ተናግረዋል።

"የፍቅርና የመቻቻል ተምሳሌት በሆነችው ድሬዳዋ ያከበርነው 16ኛው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል እውነተኛ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር ወሳኝ ሚና አበርክቷል" ያሉት ደግሞ ከአማራ ክልል የመጡት አቶ በላይነህ ወንድሙ ናቸው ፡፡

አቶ በላይነህ እንዳሉት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በብዝሃነት የደመቀ ህብረ-ብሔራዊ አንድነቱን በመጠበቅ አገርን ወደ ብልጽግና ስኬት ማድረስ አለበት፤ በተለይ በአሸባሪው ህውሃት የተጎዱ  የህብረተሰብ ክፍሎችንና አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም የመላው ኢትዮጵያውያን ትብብር ወሳኝ ነው፡፡

በድሬደዋ ከተማ አስተባባሪነት በተከበረው ቀን  ላይ የተሳተፉት  የኢፌድሪ መንግስት ፕሬዝዳንት  ሣህለወርቅ ዘውዴ በአሸባሪው ህውሃት አረመኔያዊ ድርጊት የወደሙትን አካባቢዎችና የተፈናቀሉ ዜጎች መልሶ በዘላቂነት ማቋቋም ኃላፊነት በቀዳሚነት የመላው ኢትዮጵያዊያን መሆን እንዳለበት መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም