በአፍሪካ ያለውን ሰፊ የገበያ እድል በመጠቀም በጦርነቱ ሳቢያ የሚፈጠረውን የኢኮኖሚ ጫና በዘላቂነት ለመፍታት መስራት ይገባል

54

አዲስ አበባ፣ ህዳር 30/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያለውን ሰፊ የገበያ አማራጭ በመጠቀም በጦርነቱ ሳቢያ ሊያጋጥማት የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና በዘላቂነት ለመፍታት መስራት እንዳለባት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ክቡር ገና ገለጹ።

በተጨማሪ በውጭ አገራት ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በህልውና ዘመቻው የፈጠሩትን አንድነት የኢኮኖሚ ጫናውን ለማካካስ መጠቀም እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡

አሸባሪው የሕወሃት ቡድን ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማ አንግቦ በሰሜን እዝ የሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት በማድረስ አገሪቷን ወደ አልተፈለገ ጦርነት ካስገባት ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡

በእነዚህ ጊዜያት አንዳንድ የምእራባዊያን አገራትና ለጋሽ ድርጅቶች ብድር ከመከልከል ጀምሮ ኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ ጫና የሚፈጥሩ አካሄዶችን በመከተል ዓላማቸውን ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡

በተጨማሪ ጦርነቱ በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥረው ራሱን የቻለ የኢኮኖሚ ጫና እንዳለውም እሙን ነው፡፡

የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤቶች ዋና አስተዳዳሪና የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ  ክቡር ገና ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በጦርነቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የኢኮኖሚ ጫናዎችን ለመቀነስ የተለያዩ ዘዴዎችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡

የኢኮኖሚ ማካካሻ ስራዎች ተገቢውን ጥናት መሰረት ያደረጉ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው፤ በተለይ ለአገር ውስጥ አቅም ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የተደቀነው አደጋ ለመመከት በውጭ እና አገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች  በአንድነት መቆማቸውን ጠቁመዋል፡፡

ይህንን ትብብር በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን የኢኮኖሚ ጫና ለመከላከል መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ኢኮኖሚውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሻሻል ከሚተገበሩ ስራዎች ጎን ለጎን በአፍሪካ ያለውን ሰፊ የገበያ እድል መጠቀም ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

አፍሪካ ካላት ወጣት የሰው ሃይል ቁጥር አንጻር በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቁ የገበያ መዳረሻ የመሆን አቅም እንዳላትም አብራርተዋል፡፡

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ አገራት ትልቅ እድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም