በፌዴራልና በዩኒቨርሲቲዎች ሥር በሚገኙ ሆስፒታሎች የሕክምና አገልግሎት ክፍያ ማሻሻያ ተደረገ

145

ህዳር 30/2014/ኢዜአ/ በፌዴራልና በዩኒቨርሲቲዎች ስር የሚገኙ ሆስፒታሎች የሚሰጡትን አገልግሎት ለማሳደግ የሕክምና ዋጋ ማሻሻያ መደረጉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ የስራ ሃላፊዎች የአገልግሎት ክፍያ ማሻሻያውን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

ሆስፒታሎቹ ከ40 ዓመት በላይ የሕክምና አገልግሎት ዋጋ ትመናና ክለሳ ሳያደርጉ መቆየታቸው ተገልጿል።

በሚያገኙት ገቢ መድሃኒት፣ የሕክምና መሳሪያ፣ አላቂ የሕክምና ቁሳቁስና ሌሎች ግብዓቶችን በበቂ መጠን ለማሟላት ማሻሻያው ማስፈለጉን የሚኒስቴሩ የአጋርነትና ትብብር ዳይሬክተር ዶክተር ፌቨን ግርማ ገልጸዋል።   

የጤና ተቋማቱ በወቅቱ ገበያ አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማሟላት በቂ ገቢ እያገኙ አይደለም ያሉት ዳይሬክተሯ ለሕክምና አገልግሎት የሚጠይቁት ክፍያ ከፍ እንዲል መደረጉን አስታውቀዋል።  

የተደረገው የክፍያ ማሻሻያ በመንግሥት ላይ አሁንም ጫና ያለው ቢሆንም የኅብረተሰቡን አቅም የሚጎዳ እንዳይሆን ጥንቃቄ መደረጉን ገልጸዋል።

እንደ ዶክተር ፌቨን ገለጻ የጤና ተቋማቱ ከሚጠይቁት የአገልግሎት ክፍያ 55 በመቶው በመንግሥት የሚሸፈን ሲሆን 45 በመቶው በጤና መድህን እንደሚሸፈን ታሳቢ ተደርጎ የዋጋ ክለሳ ተደርጓል።

በጤና መድህን ያልታቀፉ ዜጎች ደግሞ 45 በመቶ ወጪውን ሙሉ በሙሉ ራሳቸው የሚሸፍኑ ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል።

በመንግስትና በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ይሰጡ የነበሩ አገለግሎቶች ግን አሁንም በነጻ መሰጠታቸው ይቀጥላል ብለዋል።

የእናቶች እርግዝና ክትትል፣ የወሊድ አገልግሎት፣ የቤተሰብ ምጣኔ፣ የጨቅላ ሕጻናት፣ የጸረ ቲቢ፣ ኤች.አይ.ቪ እና ወባ ሕክምናና የስርዓተ ምግብ አገልግሎቶች በማሻሻያውም በነጻ እንዲሰጡ መወሰኑን አብራርተዋል።  

የጤና መድህን አባል ያልሆኑና ለሕክምና አገልግሎት መክፈል የማይችሉ ታካሚዎች በቀበሌያቸው በማስመስከርና የልዩ ድጋፍ የምስክር ወረቀት በማቅረብ በተዘረጋው የድጎማ ስርዓት የጤና አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉም አክለዋል።

የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረገሳ የክፍያ ማሻሻያው የጤና ተቋማቱ የሚሰጡት አገልግሎት ጥራት ያለው እንዲሆን የሚያደርግ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም