የዩኒየኑ ሰራተኞች፣ አባላትና አመራሮች የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ሰበሰቡ

121

ጎንደር፤ ህዳር 30/2014 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ የሚገኘው ፀሐይ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ሰራተኞች፣ አባላትና አመራሮች የዘማች ቤተሰቦችን የደረሰ ሰብል ሰበሰቡ።

የዩኒዬኑ ሰራተኞች፣ አባላትና አመራሮች በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ በመገኘት የዘማች ቤተሰቦችን የደረሱ ሰብሎች ሰብስበዋል።

የዩኒዬኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ይሁኔ ዳኘው ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኔኑ ለህልውና ዘመቻው ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ፣ በአይነት ደግሞ 60 ኩንታል በሶ፣ 20 ኩንታል ስኳርና 5 ኩንታል ጤፍ ድጋፍ አድርጓል።

ከደጀኑ ህዝብ ጎን በመሰለፍም የዘማች ቤተሰቦችን የእርሻ ማሳ በማረስ፣ በመዝራት በማረምና ሰብላቸውን አጭዶና ሰብስቦ በማስረከብ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዩኒዬኑ አባል አርሶ አደሮች በህልውና ዘመቻው ግንባር በመሰለፍና በደጀንነት አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ለዘማች ቤተሰቦችም ሆነ ለህልውና ዘመቻው የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ስራ አስኪያጁ አረጋግጠዋል።

''የዘማች ቤተሰቦችን መንከባከብና መደገፍ አውደ ውጊያውን የተቀላቀሉ ዘማቾች ድል እንዲቀዳጁ ከፍተኛ የሞራል ግንባታ ይሆናል'' ያሉት ደግሞ የዩኒዬኑ የቦርድ አመራር አቶ እሸቴ አለሜ ናቸው፡፡

ክቡር ህይወታቸውን መስዋዕት ለማድረግ ቤተሰባቸውን ጥለው ግንባር ለዘመቱ የሰራዊት አባላት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ የዜግነት ግዴታ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዩኒየኑም በገንዘብና በስንቅ ዘመቻውን እየደገፈ ይገኛል፡፡

አክለውም ከ100 የሚበልጡ የዩኒዬኑ ሰራተኞችና አመራሮች በምስራቅ ደምቢያ ወረዳ በመገኘት 2 ሄክታር የዘማች ቤተሰብ የጤፍ ሰብል መሰብሰብ እንደቻሉም ጠቅሰዋል።

የዩኒዬኑ ሰራተኛ ወይዘሪት አመተ ጽዮን በበኩሏ ለህልውና ዘመቻው የአንድ ወር ደመወዟን ከመስጠት ጀምሮ የዘማች ቤተሰቦችን በመንከባከብና በመደገፍ እየተሳተፈች እንደምትገኝ አመልክታለች።

''የሀገር ህልውና መከበር የመኖርና ሰርቶ የመለወጥ የህይወት ዋስትና ማረጋገጫ ጉዳይ በመሆኑ በክተት ዘመቻው የሕይወት መስዋእትነት ጭምር ለመክፈል ዝግጁ ነኝ'' ያለችው ደግሞ ወይዘሪት ትህትና በለጥካቸው ናቸው፡፡

በወረዳው የሮቢት ቀበሌ የዘማች ባለቤት ወይዘሮ አማረች ንጋቱ ''ባለቤቴ ወደ ዘመቻ ከሄደ ጀምሮ የህዝቡ ድጋፍና ትብብር አልተለየኝም'' ብለዋል።

የዩኒዬኑ ሰራተኞች ባደረጉት ጥረትም አንድ ሄክታር የጤፍ ሰብል አጭደውና ሰብስበው እንዳስረከቧቸው ገልጸው፤ ይሄም ደስታ እንደፈጠረባቸውና በወገን ድጋፍም እንዲኮሩ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

በጎንደር ከተማ የሚገኘው ፀሐይ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን 150 ሺህ አባላት ያሉት ሲሆን፤ ከ57 ሚሊዮን ብር በላይ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ወረት እንዳለውም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም