የቻይናና አፍሪካ የትብብር ጉባኤ በመጪው መስከረም መጀመሪያ በቻይና ቤጂንግ ይካሄዳል

58
አዲስ አበባ  18/2010 የቻይናና አፍሪካ የትብብር ጉባኤ በመጪው መስከረም መጀመሪያ በቻይና ቤጂንግ እንደሚካሄድ በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ታን ጂያን አስታወቁ። የኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች እንደሚታደሙበት የሚጠበቀው ጉባኤ በቻይናና አፍሪካ መካከል ያለው የትብብር ግንኙነት የሚጠናከርበትን አዲስ ስልት እንደሚቀይስ ተስፋ ተጥሎበታል። አምባሳደሩ ለአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ  እንዳሉት በቻይናና አፍሪካ መካከል የተፈጠረው የትብብር ግንኙነት በጥራትም ሆነ በውጤታማነት ወደሚሻሻልበት አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። በቤጂንግ የሚካሄደው የመሪዎች መድረክም ከፍተኛ የተግባር እርምጃዎችን በመውሰድ የሁለቱን አካላት የጋራ ፍላጎቶች ወደተጨባጭ የትብብር ስርዓት ለመተርጎም የሚያስችል ነው ብለዋል። ቻይና “ቤልትና ሮድ" በተሰኘው ኢንሼቲቭ በመላው ዓለም እየተገበረችው ያለውን የምጣኔ ኃብት ዕድገትና ኢንቨስትመንት መርሃ-ግብሯን፤ “አጀንዳ 2063” ከሚሰኘው የአፍሪካ ህብረት የልማት ውጥን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘላቂ ልማት መርሃ ግብር የአፍሪካ ግቦች ጋር ለማስተሳሰር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላትም አምባሳደሩ ገልፀዋል። ከዚህም ሌላ በፖሊሲ ቀረፃ፣ በመሰረተ ልማት፣ በንግድና ልማት ዘርፎችም ቻይና ከአፍሪካ አገራት ጋር ተቀራርባ መስራት እንደምትሻ አምባሳደሩ ጠቅሰዋል። "ከመጪው የሰለጠነ ዘመን ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ፈተናዎችን በጋራ መጋፈጥ ይቻል ዘንድ ቻይና ከአፍሪካ አገራት ጋር ጠንካራ የትብብር ግንኙነት የመገንባት ትልቅ ፍላጎት አላት" ሲሉ ነው አምባሳደር ታን ጂያን የተናገሩት። የቻይና አፍሪካ ትብብር ጉባኤ የመጀመሪያ ተባባሪ ሊቀ-መንበር ሆኖ በማገልገል ኢትዮጵያ ለመድረኩ እውን መሆን የተጫወተችውን ሚና ያነደነቁት አምባሳደር ጂያን በቻይናና አህጉሪቱ መካከል ላለው ግንኙነትም ምሳሌ መሆኗን ገልፀዋል። የቻይና አፍሪካ ትብብር ጉባኤ “ ቻይና እና አፍሪካ - በእኩል ተጠቃሚነት ላይ በተመሰረተ ትብብር ነገን የሚጋራ ጠንካራ ማህበረሰብን መፍጠር” በሚል መሪ ሀሳብ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከመጪው መስከረም 3 ቀን 2018 ጀምሮ ለሁለት ቀናት በቤጂንግ ይካሄዳል። በጉባኤው ላይ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ድርጅቶች ይሳተፋሉ። ከቻይና አፍሪካ የትብብር ጉባኤ ጎን ለጎን በሁለቱ አካላት መካከል የህዝብ ለህዝብ መስተጋብር ለመፍጠር፣ በወጣቶች፣ የአጥቢያ መንግስት አስተዳደር አካላት፣ በሲቪክ ማህበራት፣ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና የምሁራን ስብስቦች ጋር ጠንካራ የትብብር ግንኙነትን ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ የሚመክሩ መድረኮችም ይካሄዳሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም