የዳያስፖራው ወደ አገር ቤት የመግባት ፍላጎት ከፍተኛ መነሳሳት አሳይቷል

66

ህዳር 30/2014/ኢዜአ/ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጥሪ ተከትሎ በእስካሁኑ የምዝገባ ሂደት የዳያስፖራው ወደ አገር ቤት የመግባት ፍላጎት ከፍተኛ መነሳሳት የታየበት መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ገለጸ።

ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና  የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት ገብተው በዓል እንዲያከብሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መቅረቡ ይታወሳል።

በዚሁ መሰረት በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት ለመግባት ፍላጎታቸውን ማሳየታቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ገልጿል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ፤ ኢትዮጵያ የልጆቿን ትብብርና አንድነት አጥብቃ የምትሻበት ወቅት ላይ ትግኛለች ብለዋል።

ለዚህም በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጋርነታቸውን በተግባር እያሳዩ መሆኑን ገልጸዋል።

በውጭ የሚኖሩ ወገኖች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በዓልን እንዲያከብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ደክተር አብይ አህመድ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት በርካቶች ለመገኘት እስካሁን በተደረገው ምዝገባ ተነሳሽነታቸውን አሳይተዋል ብለዋል።

የዳያስፖራው ወደ አገር ቤት መግባት ለአገሩና ለወገኑ አለኝታ መሆኑን በተግባር የሚያሳይበት መልካም አጋጣሚ ስለሆነ እድሉን እንዲጠቀሙበት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።

በዚህ አጋጣሚ በዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሰሩ፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ሲሳተፉና ሲከራከሩ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንደሚመጡም ይጠበቃል ብለዋል።

በኢንቨስትመንቱ የኢኮኖሚ ጫናውን ሊደግፉ የሚችሉ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላትም እግረ መንገዳቸውን አስተዋጽዖ ሊያበረክቱ ይችላሉ ነው ያሉት።    

ኤጀንሲውም ዳያስፖራዎቹን ለመቀበል ከኤምባሲዎች፣ ከማኅበራትና ከሌሎችም አደረጃጀቶች ጋር በመሆን የምዝገባና መሰል ዝግጅቶችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአስካሁኑ የምዝገባ ሂደትም የዳያስፖራውና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት የመግባት ፍላጎት ከፍተኛ መነሳሳት የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገር ቤት ለሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ቆይታቸውን የተሳካ ለማድረግ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም