ድርጅቱ ለታርጋ ቁጥር አገልግሎት ፈላጊዎች የተቀናጀና ቀልጣፋ አሰራር ዘርግቷል

96

ህዳር 29/2014/ኢዜአ/ ከክልልና ከትራንስፖርት ቢሮዎች ለሚመጡ ለታርጋ ቁጥር አገልግሎት ፈላጊዎች የተቀናጀና ቀልጣፋ አሰራር መዘርጋቱን የፐብሊክ ሰርቪስና ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።


በቅርቡ በመንግስት ማሻሻያ ከተደረገባቸው ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች መካከል የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር አንዱ ነው።


ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በስሩ ካሉት ተጠሪ ተቋማት መካከል የፐብሊክ ሰርቪስና ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ይገኝበታል።


ከሪፎርሙ በኋላ ድርጅቱ ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር ባሻገር በትራንስፖርት ባለስልጣን ይከወን የነበረውን የተሽከርካሪ ሰሌዳ ማተም፣ ማሰራጨት፣ ማስወገድ እንዲሁም ለጠፋና ለተበላሸ ታርጋ ምትክ መስጠትን በውክልና እየሰራ ይገኛል።


የፐብሊክ ሰርቪስና ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሰለሞን አምባቸው ይህንኑ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።


በመግለጫቸውም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተደረገው የሪፎርም ስራ የተጠሪ ተቋማትን አሰራር ለማዘመን በነደፈው እቅድ መሰረት የተሽከርካሪ ሰሌዳ አገልግሎትን ድርጅቱ በጊዜያዊነት በውክልና እንዲሰራ መደረጉን አብራርተዋል።


በመሆኑም የሰሌዳ አገልግሎት አሰራርን በተቀላጠፈ መልኩ ለማከናወን ድርጅቱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በአገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።


የሰሌዳ ቁጥር አገልግሎት ከፍጥነትና ከዘመናዊ አሰራር ጋር በተያያዘ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ያሉ ተገልጋዮች ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበር አስታውሰዋል።


ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በነበረው ርክክብ አገልግሎቱን ሳይሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት በቀን ከ3 ሺህ በላይ የሰሌዳ ቁጥር ማተም ተችሏል ብለዋል።


የአገልግሎት አሰጣጡን በሚመለከት ከከተማና የክልል የትራንስፖርት ቢሮዎች ጋር በቅንጅት የሚሰራ በመሆኑ ተገልጋዮች ይህንኑ ተገንዝበው አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ ብለዋል።


የፐብሊክ ሰርቪስና ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ለመንግስት ሰራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ያለ ተቋም መሆኑም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም