በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሕዝብ አደረጃጀቶች ከክልሉ ጋር እየሰሩ ነው

56
ሶማሊያ ነሀሴ 18/2010 በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተለያዩ የሕዝብ አደረጃጀቶች ከክልላዊ መንግሥቱ ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን ገለጹ። በአካባቢው አሁን የሚስተዋለው አንጻራዊ ሠላም  በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ሠራዊት (አሚሶም) ሥር የተሰማራው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባዳረገው ጥረት ነው ብለዋል። በመሆኑም የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ከመንግሥትና ከሰላም አስከባሪ ሠራዊቱ ጋር የጋራ የሰላም ግንባታ ሥራ እንሰራለንም ነው ያሉት። በደቡብ ሶማሊያ የአገር ሽማግሌዎች ተጠሪ ማላክ ዴሎ እንደተናገሩት፤ አካባቢው አሁን ለተገኘው ሰላም የአገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ ነው። የአገር ሽማግሌዎች በአካባቢው ጎሳዎችን በማስታረቅና ወደተወለዱበት አካባቢ በማምራት እርቅ እንዲወርድ ከኅብረተሰቡ ጋር ሰርተዋል ብለዋል። የደቡብ ሶማሊያ ፕሬዝዳንት እንዲመረጥ በማድረግ በተለይም ወጣት የኅብረተሰቡን ክፍል የማረጋጋት ሥራ መሰራቱንም ገልጸዋል። በመሆኑም በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እስኪመጣና ኅብረተሰቡም ነጻ እንቅስቃሴ እስኪያደርግ ድረስ በትጋት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። የሴቶች አደረጃጀት ተወካይ ሃዋ ሶካር አሊ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሰራዊት በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ሠራዊት (አሚሶም) ሥር ከመሰማራቱ በፊት ሴቶች ላይ ችግር ይከሰት ነበር ብለዋል። ሴቶች ላይ ደብደባና የመደፈር አደጋ በአብዛኛው ይከሰት እንደነበር አስታውሰው በአሀኑ ወቅት እንዲህ ያሉ ችግሮች በእጅጉ ቀንሰዋል ነው ያሉት። ሴቶችም በመንግሥት አደረጃጀት ውስጥ ምን አይነት ሚና መጫወት እንዳለባቸው ከግምት በማስገባት ተሳትፏቸውን ለማጎልበት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። የደቡብ ሶማሊያ ፖሊስ አዛዥ መሃድ አብዱራህማን በበኩላቸው የኢትዮጵያ ጦር በስፍራው ከተሰማራ ጀምሮ አንጻራዊ ሰላም ተገኝቷል ይላሉ። "ከዚህ ቀደም አልሸባብና ኦብነግ በቀጣናው ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በማካሄድ የሕዝቡን ሰላም በእጅጉ አደፍርሰው ነበር" ይላሉ። ይሁንና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአሚሶም ሥር በመሆን ባካሄደው የሰላም ማስከበር ሥራ በአካባቢው ሠላም መምጣቱን ይጠቅሳሉ። በዚህም በተለይም የአልሸባብ ትኩረት የሆነው ወጣቱ ከመንግሥት ጋር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። የደቡብ ሶማሊያ ክልል የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሃሴን አብዲ ሞሃመድ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የተገኘው ሠላም ሕዝብና የአሚሶም ሠራዊት በጋራ ያደረጉት ጥረት ነው ይላሉ። ይሁንና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአሚሶም ከመሰማራቱ በፊትም ለሶማሊያ ሕዝቡ ካለው ቅርበት የተነሳ አዎንታዊ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል ። በዚህም አልሸባብንና መሰል የሽብር ቡድኖችን በመከላከል በአካባቢው ሰላም ለማስፈን የሰራውን ሥራ የክልሉ መንግሥት በአድናቆት ይመለከተዋል ብለዋል። የኢትዮጵያ ሠራዊት ድርቅና መሰል ችግሮች ሲከሰቱም የተለያዩ የምግብና መሰል ድጋፎችን እንደሚሰጥ ገልጸዋል። የደቡብ ምዕራብ የሶማሊያ ክልል በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በአሚሶም የኢትዮጵያ ሰራዊት ሥር ይተዳደራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም